ም/ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በቡራዩና አሸዋ ሜዳ አካባቢ በሰዎች ላይ በደረሰው ጉዳት የተሰማቸውን ሀዘን ገለፁ

በቡራዩ አሸዋ ሜዳ ባለፉት ሁለት ቀናት በሰዎች ህይወት ላይ በደረሰው ጉዳት ማዘናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ገለፁ።

በከተማ አስተዳደሩ ስም በደረሰው ጉዳት ማዘናቸውን የገለጹት ከንቲባው ጉዳቱ በታየት ያልነበረበት መሆኑን ተናግረዋል።

የከተማው ነዋሪና አስተዳደሩ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ እንደሚያደርጉና በሁሉም ነገር ከጎናቸው እንደሆኑ አስታውቀዋል።

በጉዳቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ከተማዋ መግባታቸውን የገለፁት ምክትል ከንቲባው፥ የሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

የፌዴራል፣ የከተማ አስተዳደሩና የኦሮሚያ ክልል አባላት ያሉበት ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ስራ የገባ ሲሆን፥ በጥቂት ቀናት ያለውን ነገር አጣርቶ ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ ዜጎችን ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ ያደርጋል ብለዋል።

መንግስት ከምንም ጊዜ በበለጠ ስርዓትና ህግን እንዲሁም የዜጎችን ህይወት ለመጠበቅ በኃላፊነት ይንቀሳቀሳል ነው ያሉት።

ምክትል ከንቲባው በመግለጫቸው በዚህ አይነት ሁኔታ ትርፍ ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ አካላትን ያስጠነቀቁ ሲሆን፥ ወጣቶችም የተልዕኮ ፈፃሚ መሆን እንደሌለባቸውም አሳስበዋል።

የፀጥታ አከላትም በደረሰው ጉዳት ላይ አስፈላጊውን ማጣራት ካካሄዱ በኋላ መረጃው ለህዝብ ይፋ ይሆናል ብለዋል።

መንግስት በጥቃቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እጃቸው ባስገቡ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ አስፈላጊው ማጣራት ከተካሄደ በኋላ እርምጃ እንደሚወሰድም አስታውቀዋል።(ኤፍ.ቢ.ሲ)