በቡራዩና አካባቢው ለንጹሃን ሞትና ንብረት ውድመት ተጠያቂ ናቸው ተብለው የተያዙ ተጠርጣሪዎች ቁጥር 200 ደረሰ

በቡራዩና አካባቢው የሰው ህይወት በማጥፋትና ንብረት በማውደም ተጠርጥረው የተያዙ ግለሰቦች ቁጥር 200 መድረሱን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለማየሁ እጅጉ አስታወቁ፡፡

ችግር ፈጥረዋል የተባሉ ግለሰቦችንም ተከታትሎ በቁጥጥር ስር ለማዋል በህዝብ ጥቆማ እየተደረገ እንደሚገኝም ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል፡፡

ኮሚሽነሩ በቡራዩና ከታ ትናንትናና ዛሬ ምንም ዓይነት ትንኮሳ ያለመኖሩንም ገልጸዋል፡፡

እስከአሁን ድረስ የሟቾቹ ቁጥር ትናንት እንደተነገረው 23 መሆኑን ጠቅሰው ምናልባት የሟቾቹ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽነሩ ተጨማሪ የጸጥታ ኃይል መመደቡን ጠቅሰው በየቦታው የተዘረፈውንም ንብረት የማስመለስ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

አሁን ያለው ነገር እየተረጋጋ በመሆኑ ነዋሪው አካባቢውን ለቆ እንዳይወጣ የወጡትም እንዲመለሱ ጥረት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

እስከአሁን የተፈጸመው ድርጊት የሚያሳዝን መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ ጥቃቶች ዳግም እንዳይፈጸሙ የጸጥታ ኃይሉ በተጠንቀቅ መቆሙንም ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽነሩ በመጨረሻም ነገሮች እንዲባባሱ ከማድረግ ነገሮች እንዲቀዘቅዙ ሰው ወደ ሰላሙ እንዲመለስ የሁሉም ኃላፊነት መሆን ይገባዋል በማለት አሳስበዋል፡፡(ኤፍ.ቢ.ሲ)