ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ሰላም ትልቅ አስተዋጽኦ በማድረጓ አድናቆት እንደሚገባት አምባሳደር ሞርጋን ተናገሩ

ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን  ተቀናቃኝ  ኃይሎች መካከል የፊት ለፊት  ድርድር እንዲካሄድና በአገሪቱ  ዘላቂ  ሰላም  እንዲሰፍን ላደረገችው አስተዋጽኦ ታላቅ አድናቆት እንደሚገባት በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን ገለጹ ።

አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን ከዋልታ ቴሌቭዠን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በደቡብ ሱዳን ዋነኛ  ተቀናቃኞች ኃይሎች የሆኑት  ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪርና የቀድሞ ምክትላቸው ሪክ ማቻር መካከል ቀጣይነት የሰላም ድርድር  እንዲካሄድ  ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል ።

የደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር ሂደት ስኬታማ እንዲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ተከታታይ  ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱንም  የጠቆሙት  አምባሳደሩ ጠቁመዋል ።

እንደ አምባሳደር ሞርጋን ገለጻ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብ  በምስራቅ አፍሪካ በተለይም በደቡብ ሱዳን  አዲስ የሰላም ፣ የልማት፣ የዕድገትና የብልጽግና ምዕራፍ እንዲከፈት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ   ነው ብለዋል ።                    

 እ.ኤ.አ  በመስከረም 12 ፤ 2018  ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪርና የቀድሞ ምክትል ፕሬዚደንት ሪክ ማቻር ሰላምን  ለማምጣት ስምምነት ላይ የደረሱ ቢሆንም  ከዚህ ቀደም ተቀናቃኝ ኃይሎቹ 16 ጊዜ የሰላም ስምምነቶቹ  መጣሳቸው ያስታወሱት አምባሳደር ሞርጋን የሳለም ስምምነቶቹ ተግባራዊ ያልሆኑት  በጥቂት ፀረ-ሰላም ኃይሎች ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል ።

 በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች መካከል የተደረሰው ስምምነት ተግባራዊ መሆን  ከጀመረም ከደቡብ ሱዳን የተሰደዱ ዜጎችን መልሶ ማቋቋምና የመሠረተ ልማት መገንባት እንዲሁም ምርጫ ማካሄድ  የመንግሥት ቀዳሚ  ተግባር እንደሚሆኑ አምባሳደር ሞርጋን ተናግረዋል ።    

የተለያዩ  ምንጮች እንደሚገልጹት ባለፉት ዓመታት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ደቡብ ሱዳንያውያን ለዓመታት  በተፈጠሩት  ግጭቶች  ምክንያት ከመኖሪያ  ቀያቸው  መፈናቀላቸው  ይታወቃል ።

በመጨረሻም አምባሳደር ሞርጋን ጀምስ አዲሱ  ዓመት  ለመላ ኢትዮጵያውያን በሙሉ  የስኬትና የብልጽግና እንዲሆን ተመኝተዋል  ።