በኦሮሞ ህዝብ ስም የተደራጁ ፓርቲዎች ለህዝብ ተጠቃሚነት በአንድነት መስራት ይጠበቅባቸዋል- ር/መስተዳድር ለማ መገርሳ

በኦሮሞ ህዝብ ስም የተደራጁ የተለያዩ የፓለቲካ ፓርቲዎች የተጀመረውን ለውጥ በማስቀጠል በአንድነት መስራት እንዳለባቸው የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳር አቶ ለማ መገርሳ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በኦህዴድ ድርጅታዊ ጉባዔ የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት በህዝቡ ስም የተደራጁ የፓለቲካ ፓርቲዎች መከፋፈል በህዝቡ አንድነት ላይ ከባድ አሉታዊ ተፅዕኖ ያለው በመሆኑ በልዩነቶቻቸው ዙሪያ በመነጋገር በአንድነት መስራት እንደሚገባችው አሳስበዋል።

የህዝብን ጥቅም በሚያስከብሩ ጉዳዮች ላይ በአንድነት መስራት እንሚያስፈልግ ገለፀዋል።

የተለያዩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተራርቆ ከመታገል በጠረጴዛ ዙሪያ ወደ መነጋገር በተሸጋገርንበት ወቅት የሚካሄድ በመሆኑ ጉባዔ የተለየ ያደርገዋል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በአሁን ወቅት ለተገኘው ለውጥ በሀገር ውስጥና በውጭ ሆነው የተለያየ ሚና የነበራቸው አካላት ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

በ9ኛው የኦህዴድ ጉባዔ ያለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት የድርጅቱ አፈፃፀም የሚገመገምበት፣ድክመትና ጥንካሬው የሚለይበት እና የተጀመረው ለውጥ ማስቀጠል የሚችል መሆኑን ገልጸዋል።

ኦህዴድ በርካታ ውጣ ውረዶችን መሻገሩን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ሂደት ውስጥ ክልሉና ሀገሪቷን የሚጠቅምና ፓለቲካውን ወደ አዲስ መንገድ የሚያሻግር ስራዎችን ተግባራዊ እድርጓል ብለዋል።

በዚህም በፓለቲካ አመለካከታቸው ከሀገር ወጥተው የነበሩ ፓለቲከኞች፣ አክቲቪስቶችና ጋዜጠኞች ወደ ሀገራቸው በመግባት በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉበት እድል መፈጠሩን ጠቁመዋል።

እንዲሁም በፓለቲካዊ አመለካከታቸው በእስር ቤት የነበሩ ወጣቶች፣ ፖለቲከኞችና ሌሎች አካላት ከእስር ቤት እንዲወጡ ኦህዴድ መታገሉን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።(ኤፍ.ቢ.ሲ)