9ኛው የኦህዴድ ጉባኤው ዛሬም ቀጥሎ እየተካሄደ ሲሆን በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ውይይት እየተደረገ ይገኛል ።
የኦህዴድ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ለተደረገው ውይይት ማጠቃሊያ ሠጥተዋል ።
ዶክተር አብይ እየተካሄደው ባለው ጉባኤ ላይ እንደገለጹት የኦህዴድ ሆነ ኦሮሞ ድል አደረገ የሚባለው ለኢትዮጵያ አንድነት ግንባታ ሲሠራ ነው ብለዋል ።
አሁን በተገኘው ድል ከመኩራራትና እርስ በእርስ ከመጣላትም ለቀጣይ ድል መዘጋጅትና መሥራት እንደሚገባ ዶክተር አብይ በጉባኤው ተናግረዋል ።
የሐሳብ አሸናፊነትና መልካም ተጽዕኖን መፍጠር የሚቻለው በጥንታዊ የገዳ ሥርዓት ደንብ በሚያዘው መሠረት ሁሉንም የአገሪቱን ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን የምናቅፍ ሲሆን ብቻ ነው ብለዋል ዶክተር አብይ በንግግራቸው ።
ጠላቶቻችን የሚያውጁብንን ጦርነት ለመቋቋም እርስ በእርስ በመደማመጥ አንዱ ሌላውን በመደገፍ የተጀመረውን ጉዞ ማስቀጠል እንደሚገባ ዶክተር አብይ ተናግረዋል ።
ስትራቴጂካዊ የትግል ስልትና ጠንካራ አደረጃጀት ካለም የሚያጋጥሙ ፈተናዎች ለመቋቋም ያግዛል ብለዋል ዶክተር አብይ ።
በአገሪቱ አሁን የተጀመሩት አይነት የዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች ባለፉት ዓመታት ቢከናወኑ ኖሮም ኡን እየታየ ያለውን ዓለምን ያስደመመ የዲፕሎማሲ ስኬቶችን መፍጠር ይቻልም እንደነበር ዶክተር አብይ በቁጭት ተናግረዋል ።
የጉባኤው ተሳታፊዎች ከመሥመር የመውጣት ፣ መተራረም ላይ ክፍተት በመስተዋሉና ይህም ለጉዞው ቀጣይነት እንቅፋት በመሆኑ ትኩረት ተሠጥቶበት ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል ።
በጉባኤውም ጠንካራ ወጣት አመራሮች ወደፊት ለማምጣት ምርጫዎች ይካሄዳሉም ተብሏል ።
በጅማ ከተማ እየተካሄደ ባለው የኦህዴድ 9ኛ ጉባኤ ለውይይት የቀረቡት አጀንዳዎች በሙሉ ተግባራዊ እንዲደረጉ በሙሉ ድምጽ ፀድቀዋል ።
ጉባኤው በትናንትና ከሰዓት ውሎው የፕሬዚዲየም ኮሚቴ አባላት ምርጫ አካሄዷል ።
በትናንትናው ዕለት ምርጫውም ዶክተር አብይ አህመድ በኦህዴድ ሊቀመንበርነትና ሥራ አስፈጻሚነት ፣ አቶ ለማ መገርሳ በምክትል ሊቀ መንበርነትና ሥራ አስፈጻሚነት ፣ ዶክተር ወርቅህ ገበየሁ የኦህዴድ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የኦህዴድ ማእከላዊ ጽህፈት ቤት ሀላፊ በመሆን ተመርጠዋል ።