በቡራዩ ግጭት ህይወት በማጥፋትና ዝርፊያ በመፈፀም የተጠረጠሩ ከ200 በላይ ግለሰቦች ዛሬፍርድ ቤት ቀርበዋል

የአዲስ አበባ ፖሊስና የኦሮሚያ ፖሊስ በቡራዩ ከተማና አካባቢዋ በደረሰው የሰው ህይወት መጥፋት የአካል ጉዳት፣ ዘረፋና ንብረት እጃቸው አለበት ብለው የጠረጠሯቸው ከ200 በላይ  ግለሰቦች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ እያከናወነ የሚገኝባቸው ብርሃኑ ታከለ፣ ሸዋንግዛው ሾሺ፣ መሀመድ ሀሰን፣ መኮንን ለገሰ፣ ጫሚሳ አብዲሳ፣ መንግስቱ ዋቁማ እና ገመቺስ አበረ የተባሉ ተጠርጣሪዎች ከአዲስ አበባ በተሽከርካሪ በመመላለስ የቡራዩ ግጭትን በማስተባበር፣ በማነሳሳት እና ገንዘብ በማከፋፈል መጠርጠራቸውን መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል።

የጀመረውን ምርመራ ተጨማሪ ሰነዶችን ለማሰባሰብ የ14 ቀን ጊዜ ይሰጠኝ ሲልም ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው በጨለማ ቤት ተዘግቶብን ነው ያለነው፤ እየተጉላላን ነው በመሆኑም በዋስ ልንወጣ ይገባል ሲሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

ተጠርጣሪዎቹ የቀረቡበት የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19 ወንጀል ችሎት ዛሬ ከሰዓት በኋላ የሁለቱንም ጉዳይ በማየት ለተጨማሪ ምርመራ ለፖሊስ የ14 ቀን ጊዜ ፈቅዷል።

የኦሮሚያ ፖሊስ በበኩሉ ጠዋት 35 ተጠርጣሪዎችን በቡራዩ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎት አቅርቦ የ14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ የጠየቀባቸው ሲሆን፥ ፍርድ ቤቱም እያንዳንዳቸው የፈፀሙትን ድርጊት በተናጠል እና በዝርዝር መርምሮ ለመስከረም 25 እንዲያቀርብ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

መርማሪ ፖሊስ ከሰዓት በነበረው ችሎትም 219 ተጠርጣሪዎችን ፋይል የከፈተ ሲሆን፥ ችሎቱ ካለው የቦታ ጥበት አንፃር በየተራ እየተመለከተ ይግኛል።

የተጠርጣሪዎች የእምነት ክህደት ቃልንም በመቀበል ላይ ይገኛል።

ከቡራዩ ግጭት ጋር ተያይዞ ዛሬን ጨምሮ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው የሚገኙ እና የክልሉ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ሰዎች ቁጥር 364 ደርሷል።(ኤፍ.ቢ.ሲ)