አስተዳደሩ ለዓመታት ታጥረው የተቀመጡ ከ4 ነጥብ 1 ሚሊየን ካሬ ሜትር በላይ መሬት ውል እንዲቋረጥ ወሰነ

ከ1997 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ታጥረው የቆዩ 154 ቦታዎች 4 ሚሊየን 126 ሺህ 423 ካሬ ሜትር መሬት የሊዝ ውላቸው ተቋርጦ ለህዝብ ጥቅም ተመላሽ እንዲሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ወሰነ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለረጅም ጊዜ ታጥረው የተቀመጡ  እነዚህ  ቦታዎች በመንግስት፣ በግል ባለሀብቶችና በተለያዩ የዲፕሎማቲክ ተቋማት ተይዘው የነበሩ ናቸው ።

የአስተዳደሩ ካቢኔ ዛሬ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረትም በድምሩ 154 በተለያዩ የከተማዋ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ቦታዎች ለህዝብ ጥቅም ተመላሽ ይደረጋሉ።

ቦታዎቹም፦

በግል ባለሀብቶች  የተያዙ 95 ቦታዎች፦  456,428 ካሬ  ሜትር

በመንግስት መስሪያ ቤቶች የተያዙ 19 ቦታዎች፦ 127,140.93 ካሬ ሜትር

የሸራተን ማስፋፊያን ጨምሮ በሚድሮክ ግሩፕ የተያዙ 11 ቦታዎች፦ 549,241.ካሬ ሜትር

በዲፕሎማቲክ ተቋዋማት የተያዙ 18 ቦታዎች፦  250,413.89  ካሬ ሜትር

በፌደራል ተቁዋማት መከላከያና ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ 11 ቦታዎች፦ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ካሬ ሜትር

በአጠቃላይ 154 ቦታዎች በካሬ 4,126,423.83/ አራት ሚሊየን አንድ መቶ ሀያ ስድስት ሺህ አራት መቶ ሀያ አራት ካሬ የሊዝ ውላቸው ተቋርጦ ተመላሽ እንዲሆኑ ተወስኗል።

ቦታዎቹ ከ 1997 እስከ 2004 በተለዬዩ ጊዜያት የተላለፉና እስካሁን ምንም አይነት ልማት ሳይከናወንባቸው ታጥረው የተቀመጡ መሆናቸውን አስተዳደሩ አስታውቋል።

የካቢኔ ስብሰባውን የመሩት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ እነዚህና መሰል ቦታዎች የከተማዋን ልማት እንዲጓተት ምክንያት እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

ይህ ስራ የአንድ ጊዜ ዘመቻ ሳይሆን ከዚህ በኋላ መስተዳድሩ ቦታ ወስደው ወደ ልማት የማይገቡ ማንኛውም የመንግስትም ሆነ የግል ባለሀብት ላይ ጥብቅ ክትትል አድርጎ እርምጃ እንደሚወስድ ነው ያስታወቁት።(ኤፍቢሲ)