የኢትዮጵያና የግብፅ ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በኢትዮጵያ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የግብፅ አምባሳደር አቡበከር ሄፍኒ ማህሙድን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ሸኝተዋል  ፡፡

ዶክተር ወርቅነህ የኢትዮጵያና የግብፅ ግንኙነት በመሪዎቻቸው በሳል አመራር አማካኝነት ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን ተናግረዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከምንጊዜውም በላይ በመተማመንና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ 

ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ አምባሳደሩ በኢትዮጵያና ግብፅ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ድልድይ ሆነው እንደሚያገለግሉ እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡

አምባሳደር አቡበከር በኢትዮጵያ  ቆይታቸው ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መጎልበት ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን ዶ/ር ወርቅነህ አቅርበዋል፡፡

አምባሳደር አቡበከር  በበኩላቸው በስራ ቆይታቸው  የኢትዮጵያ መንግስት ላደረገላቸው እገዛ አመስግነው፣ የሁለቱ አገሮች የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ትብብር  ወደ ከፍተኛ ደረጃ  መሸጋገር እንዳለበት ገልጸዋል ፡፡

ኢትዮጵያና ግብፅ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማስፋት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡