11ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በጥር ወር የመጀመሪያ ሳምንት ይከበራል

11ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በጥር ወር የመጀመሪያ ሳምንት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን  በጠበቀ መልኩ በመላ አገሪቱ የሚከበር  መሆኑ ተገለጸ ።   

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ በዛሬው ዕለት በሠጡት መግለጫ እንደገለጹት 11ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን   በተመሳሳይ ሰዓት  በአገሪቱ በሚገኙ ክልሎች ፣ የመንግሥት ተቋማትና ህዝባዊ  ተቋማት  በሙሉ  የሚከበር  መሆኑን ተናግረዋል ።

የዘንድሮ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል “ ሰንደቅ ዓላማችን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችን” በሚል መሪ ቃል ለ11ኛ ጊዜ ይከበራል ብለዋል  ወይዘሮ ሽታዬ ።

በአገሪቱ  አሁን ባለው ለውጥ ሂደት ውስጥ ከሰንደቅ ዓላማ ጋር በተያያዘ  የተለያዩ ጥያቄዎች እየተነሱ ስለመሆኑ የጠቆሙት  ወይዘሮ ሽታዬ  የሰንደቅ ዓላማ ቀን  ከመከበሩ አስቀድሞ  የተለያዩ  የህብረተሰብ ክፍሎች  በሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ  ላይ ለማወያየት መድረክ የሚዘጋጅ  መሆኑን አስረድተዋል  ።

በተለይም  ወጣቶች  በኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች እንደሚካሄዱም  ወይዘሮ ሽታዬ በመግለጫቸው አስታውቀዋል ።

ሁሉም ዜጎች ስለሰንደቅ ዓላማ ያላቸውን ጥያቄዎች  በዴሞክራሲያዊ አግባብ ፣ የህግ የበላይነትን  በጠበቀ መልኩ ብቻ  ማንሳትና ለሚመለከተው አካል  ማቅረብ እንደሚችሉ ወይዘሮ ሽታዬ በመግለጫው ተናግረዋል ።

የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ሁሉም በኃላፊነት ስሜት  በዓሉን እንዲከበር  የበኩሉን  አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ምክትል አፈ ጉባኤዋ ጥሪ አድርገዋል ።

የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት በሥራ ላይ ያለው ሰንደቅ ዓላማ የአገሪቱ ሉዓላዊነት መገለጫ መሆኑን ባስቀመጠው መሠረት  አገር አቀፍ  የሰንደቅ ዓላማ  በዓል በየዓመቱ እየተከበረ  ይገኛል ።