የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከተመድ ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬወዝ ጋር ተወያዩ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒቶ ጉሬቴዝ ጋር በአሜሪካ ኒው ዮርክ ተወያዩ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እና የተመድ ዋና ፀሃፊ አንቶኒቶ ጉሬቴዝ በኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው 73ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን ነው ተገናኝተው የተወያዩት።

በነበራቸው ቆይታም በአሁኑ ወቅት በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና እየታዩ ባሉ ተስፋ ሠጪ ተግባራት ዙሪያ እና ቀጣይ ፈተና የሚሆኑ ጉዳዮችን እንዴት መፍታት ይቻላል የሚለው ላይ ተወያይተዋል።

የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒቶ ጉሬቴዝ በዚሁ ወቅት፥ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተጀመረውን ግንኙነት አድንቀው፤ ሁለቱ ሀገራት የጀመሩት ግንኙነት ለምስራቅ አፍሪካ ሰላም እና መረጋጋት የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል። 

ኢትዮጵያ በኤርትራ እና በጂቡቲ መካከል ሰላም እንዲሰፍን ለጀመረችው የማግባባት ስራም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስፈላጊውን ድጋፍ በሙሉ ለመሥጠት ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል።

በተያያዘ ዜና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ በተመድ የፀረ ሽብር ቢሮ ዋና ፀሃፊ ቨላድሚር ቮሮንኮቭ ጋርም በኒው በዮርክ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ኢትዮጵያ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በምን መልኩ መተባበር አለባቸው የሚለው ላይ ሀሳብ ተለዋውጠዋል።(ኤፍ.ቢ.ሲ)