ኢትዮጵያ ፣ሱዳንና ግብጽ በህዳሴው ግድብ ውሃ አሞላል ጥናት ላይ እየተወያዩ ነው

የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የውሃ ሚኒስትሮች በህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል ዙሪያ ባለሙያዎች ያደረጉትን  ጥናት ሪፖርት ካዳመጡ በኋላ  ውይይት እያደረጉ መሆኑ ተገለጸ ።
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል ዙሪያ የተቋቋመው የገለልተኛ ባለሙያዎች ቡድን ያቀረቡትን ጥናት  ሪፖርት መሠረት በማድረግ  የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የውሃ ሚኒስትሮች በአዲስ አበባ ውይይት እያደረጉ ይገኛሉ።
የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ የሱዳን የውሃ ሃብት፣ የኤሌክትሪክና የመስኖ ሚኒስትር ኢንጂነር ከድር ጋስመዲን እና የግብፅ የውሃ ሃብትና የመስኖ ሚኒስትር ዶክተር መሀመድ አብዱላቲ እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የሶስቱ ሀገራት መሪዎች የግድቡ ውሃን  እንዴት መለቀቅ አለበት በሚለው ጉዳይ  ጥናት  የሚያደርገው  ቡድን እስካሁን የደረሰበትን  የውጤት ሪፖርት በማድመጥ ቀጣይ አቅጣጫ ላይ  ውይይት እያደረገ ይገኛል።
የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፥ የተመራማሪዎቹ ቡድን እስካሁን ሥራውን በጥሩ ሁኔታ እያከናወነ መሆኑንና   ጥናቱ  ለወደፊቱ  በሦስቱ  አገራት  የሚደረገውን ውይይት የተሳካ ያደርገዋል ብለው እንደሚጠብቁ ጠቁመዋል።
የግብፅ የውሃ ሀብትና የመስኖ ሚኒስትር ዶክተር መሐመድ አብዱላቲ፥ በሁለቱ ጥናቶች ሂደት ላይም ሆነ በባለሙያዎች የስራ አፈፃፀም ሂደት ላይ ልዩነቶች ቢኖሩም፤ በውይይት እንደሚፈቱ የሚጠቁም ንግግር አድርገዋል።
የሱዳን የውሃ ሀብት፣ የኤሌክትሪክና የመስኖ ሚኒስትር ኢንጂነር ከድር ጋስመዲን በበኩላቸው፥ ማንኛውንም ልዩነቶችን በቅን ልቦና ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውንና በግድቡ ዙሪያ  በተሻለ ስምምነትና እልባት ላይ ይደረሳል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል  ።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ  ተጽዕኖ ግምገማ  ለማድረግ  ከሶስቱ ሀገራት የተውጣጡት ተመራማሪዎችን ያካተተው የባለሙያዎች ቡድን ከሶስት  ወራት  በፊት  የተቋቋመ መሆኑ  ይታወቃል  ።