ከጋሞ ሽማግሌዎች ኢትዮጵያዊያን ብዙ ሊማሩ ይገባል- አቶ ለማ መገርሳ

ተንበርክከው ህብረተሰቡን ከጥፋት ከታደጉት የጋሞ ሽማግሌዎች ኢትዮጵያውያን ብዙ ሊማሩ እንደሚገባ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ገለጹ።  

የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ትላንት ማምሻውን ከጋሞ ሽማግሌዎች ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው ይህንን የተናገሩት።

በውይይቱ ወቅትም ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ፥ የጋሞ ሽማግሌዎች በአርባ ምንጭ በሚኖሩ የኦሮሞ ተዋላጆች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ እና በንብረታቸው ላይ ጥቃት እንዳይፈፀም በማድረግ ታላቅ ስራን ሰርተዋል ብለዋል።

የጋሞ ሽማግሌዎች የሰሩት ስራ ህይወት ከመታደግም በላይ ለሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች እና ሽማግሌዎች ትልቅ ትምህረት የሚሰጥ ነው ያሉት አቶ ለማ የጋሞ ሽማግሌዎች ለፈፀሙት ታላቅ ተግባርም ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

የጋሞ ሽማግሌዎች በበኩላቸው፥ ከኦሮሞ ወንድሞቻችን ጋርም ይሁን ከሌሎች የኢትዮጵያ ወንድሞቹ ጋር ፀብ የለውም፤ በፍቅር ነው የኖረው ሲሉ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም በቡራዩ ከተማ እና አካባቢው የተፈጠረው ችግር አንዲፈታም ከአባ ገዳዎች ጋር በመስራት እርቅ እንዲፈጠር እንሰራለን ሲሉም አስታውቀዋል።

በቡራዩ እና አካባቢው የተከሰተውን ችግር አስመልክቶ እና ከአካባቢው የተፈናቀሉ ዜጎች የተመለሱበትን አግባብ አስመለክቶም ለርእሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ ጥያቄ አቅርበዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው፥ በቡራዩ እና አካባቢው ተፈጥሮ የነበረው ችግር በምንም መመዘኛ የኦሮሞን ህዝብ የማይወክል መሆኑን አነስተው፤ ተግባሩም የወንጀለኞች ስራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ከቡራዩ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው የመመለሱና ጥፋተኞችን ለህግ የማቅረቡ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ርእሰ መስታደድሩ ገልጸዋል።

ተፈናቃዮችን ወደ መኖሪያቸው ከመመለስ ጋር ተያይዞ ሀላፊነት የጎደለው ስራ አይሰራም ያሉት አቶ ለማ፥ ምን  አይነት ጉዳት ደረሰባቸው የሚለው ከተለየ በኋላ ነው እንዲመለሱ የተደረገው ብለዋል።

ርእሰ መስተዳድሩ አቶ ለማ መገርሳ፥ ቤት ነብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች እንዲመለሱ አልተደረገም፤ በቀጣይ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር እየተሰራ እንዲመለሱ ይደረጋልም ሲሉም ተናግረዋል።

የጋሞ ሽማግሌዎች ያነሱትን የእርቅ ጉዳይ በተመለከተም፥ በቅርቡ ከአባገዳዎች ጋር ውይይት በማድረግ እርቀ ሰላሙ እንዲፈፀም ይሆናል ብለዋል።

ሆኖም ግን ግጭቱ በእርቀ ሰላም ብቻ እልባት አያገኝም፤ የሁለቱን ህዝቦች ለማቃረን ግለሰቦች ያራመዱት አጀንዳ በመሆኑ ተጠያቂዎችን ለህግ የማቅረብ ስራ ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል ሲሉም ተናግረዋል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)