ብአዴን በ12ኛው ድርጅታዊ ጉባኤው ለውጥንና አንድነትን የሚያጠናክሩ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ብለን እንጠብቃል- እህት ድርጅቶች

ብአዴን በ12ኛው ድርጅታዊ ጉባኤው ለውጥንና አንድነትን የሚያጠናክሩ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ብለን እንጠብቃል ሲሉ የብአዴን እህት ድርጅቶች ገለጹ።

በጉባኤው ላይ የተገኙት የኦዴፓ ማዕከላዊ ከሚቴ ጽህፈት ኃላፊ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የብአዴን 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ እንደ ሀገር በአዲስ መታደስና አዲስ ለውጥ በተጀመረበት ጊዜ የሚካሄድ ታሪካዊ ጉባኤ ነው ብለዋል።

በዚሁ ጉባኤ ብአዴን አንድ ድርጅት የድርጅቱ እና የሃገሪቱን መጻይ እድል የሚወስኑ ውሳኔዎች እንደሚያሳልፍም ገልጸዋል።

ለአማራና ኦሮሚያ ክልል ህዝቦች አብሮነትና አንድነት መጠናከር ኦዴፓ ከብአዴን ጋር አብሮ እንደሚሰራም የተናገሩት ወይዘሮ አዳነች፥ የሁለቱ ክልሎች ህዝቦችን ግንኙነት የበለጠ እንደሚጠናከር ገልጸዋል።

አሁን ላይ ሀገሪቱ ህዝቦች የአንድነትና ህብረት ለውጡን በጫነች የፍቅር መርከብ ላይ መሣፈራቸውንም ገልጸዋል።

ብአዴን የሀገሪቱን ህዝቦች አንድነት የሚያጠናክሩ ውሳኔዎችን እንደሚያስተላልፍ እና በውሳኔዎች አቅጣጫና አተገባበር ሂደት ኦዴፓ ከጎኑ እንደሚሰለፍም ነው ወይዘሮ አዳነች የተናገሩት።

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ ድርጅታቸውን በመወከል ባስተላለፉት መልዕክት 12ኛው የብአዴን ድርጅታዊ ጉባዔ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ዳር ለማድረስ ትልቅ ሚና አለው ብሎ ድርጅታቸው ህወሓት እንደሚያምን ተናግረዋል።

የህዝብ ለህዝብ ቁርኝቱን ይበልጥ ለማጠናከር ህወሓት ከብአዴንና ከአማራ ህዝብ ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ ነው ያሉት አቶ ጌታቸው፥ በህዝቦቻችን መካከል መጠራጠር እንዳንፈጥር መጠንቀቅ ይኖርብናል ብለዋል።

አልፎ አልፎ በአማራና በትግራይ ህዝቦች መካከል ልዩነት ለመፍጠር የሚደረገው ሙከራ ሊወገዝ እንደሚገባውም አሳስበዋል።

ብአዴን ከ12ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ የክልሉን ህዝብ የተጠቃሚነት ጥያቄ ጭምር የሚያረጋግጡና ለውጡን የሚያጠናክሩ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ እና ህወሀትም ከብአዴን ጋር በጋር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የደኢህዴን ተወካይ የሆኑት ወ/ሮ አልማዝ መሰለ በበኩላቸው ብአዴን የአማራ ክልል ህዝብ ባለፉት ስርዓቶች የሰብዓዊና ዴሞክራሲ መብት ረገጣን በተደራጀና ባልተደራጀ መንገድ በማታገል ስርዓቱን ለመገርሰስ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።

ድርጅቱ ይህንን ለውጥ በማስቀጠል እኩልነትና ፍትሃዊነት እንዲረጋገጥ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያብብ ከፍተኛ ድርሻ ያለው መሆኑንም ነው የተናገሩት።

12ኛ የብአዴን ድርጅታዊ ጉባኤ በበርካታ ድሎችና ስጋቶች ታጅቦ የሚከናወን መሆኑን የተናገሩት ወ/ሮ አልማዝ፥ አሁን ላይ ሀገሪቱ እያስተናገደች ያላችውን ፈጣን ለውጥ የሚያስተናግዱ አሰራሮችን መቀየስ አስፈላጊ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ቀደም ሲል የኢህአዴግና እህት ድርጅቶች ከህዝቦች ጋር የነበራቸውን የትስስር መላላት ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም ብአዴን ድሎችን በማጠናከርና ዘላቂ ለማድረግ የላቀ ለውጥ ለማስመዝገብ በሚያከናውናቸው ተግባራት ደኢህዴን ከብአዴን ጎን አብሮ የሚሰለፍ መሆኑን አረጋግጠዋል።(ኤፍ.ቢ.ሲ)