በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፀረ-ሰላም ኃይሎች ባደረሱት ጥቃት አራት ሰዎች ህይወት አለፈ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን ጸረ ሰላም ኃይሎች ትናንት ባደረሱት ጥቃት የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የክልሉ ፓሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ሰይፈዲን ሀሩን ድርጊቱን አስመልክቶ በሠጡት መግለጫ እንዳሉት የጥፋት ኃይሎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ኦሮሚያ ክልሎች መካከል በሚገኘው "ኪንግ ካማሽ" በተባለ ሥፍራ በጦር መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ፈጽመዋል፡፡

ኮሚሽነር ሰይፈዲን ሀሩን ጥቃቱ የደረሰው በክልሉ ካማሽ ዞን እና በአጎራባች የኦሮሚያ ክልል ተከስቶ የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት የማረጋጋት ሥራ ሰርተው ወደ ካማሽ ሲመለሱ በነበሩ የዞኑ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በጥቃቱ በመንግስት ተሸከርካሪ ውስጥ ሲጓዙ ከነበሩ ሰባት ሰዎች መካከል የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉንና ንብረት መውደሙንም ነው ያነሱት፡፡

ሰሞኑን የተከሰተውን ውጥረት ተከትሎ መስከረም 16 በካማሽ ዞን ፖሊስ ግቢ ውስጥ የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤት ላይ የዘረፋ ሙከራ መደረጉን ኮሚሽነር ሰይፈዲን አያይዘው ጠቅሰዋል፡፡

ፖሊስ የዘረፋ ወንጀል ሊፈጽሙ የነበሩትን ለመያዝ ምርመራ እያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ በክልሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የታየው ተደጋጋሚ የጸጥታ ችግር በሕብረተሰቡ ማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እየፈጠረ ያለበት ሁኔታ ተስተውሏል ፡፡

አካባቢውን ለማረጋጋት በተደረገው ጥረት የሀገር መከላከያ፣ የፌደራል ፖሊስ እንዲሁም የሁለቱ ክልሎች የፀጥታ ኃይሎች ቅንጅት በመፍጠር የጎላ ሚና እየተጫወቱ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

" ከችግሩ በስተጀርባ ክልሉም ሆነ በአጠቃላይ ኢትዮጵያን የማናጋት አጃንዳ ያላቸው አካላት አሉ " ያሉት ኮሚሽነሩ ህብረተሰቡ ይህን በመረዳት የራሱን ሰላም ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በአሁኑ ወቅትም በፖሊስ በኩልም ህብረተሰቡን የማረጋጋት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡