የዘንድሮው የመስቀል በዓል በድምቀት መከበሩን ጽህፈት ቤቱ ገለጸ

የዘንድሮው የመስቀል በዓል ከወትሮው በተለየ በድምቀት መከበሩን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ገለጸ።

ጽህፈት ቤቱ በሳምንታዊ የአቋም መግለጫው “ደመራ የመደመር በዓል እንደሆነው ሁሉ መደመር አንዱ ከሌላው ጋር የሚያያዝበት እንጂ የሚለያይበትና የሚከፋፈልበት ባለመሆኑ ለአንዲት አገር ግንባታ በአንድነት እንድንቆም በዓሉ ትልቅ መልዕክት ተላልፎበታል” ብሏል።

ኢትዮጵያ የጀመረችው የይቅርታ፣ የፍቅር፣ የመደመርና የአንድነት ጉዞ ፍሬ ለኢትዮጵያውያን እጅግ አጓጊና ብሩህ ተስፋ ፈንጣቂ ከመሆን ባለፈ የቅርብ ጎረቤትና የሩቅ ወዳጅ አገሮችን ጭምር በትኩረት የሚከታተሉት እንደሆነ ገልጿል።

በተያያዘም የኢሬቻ በዓል በመጪው እሁድ በቢሾፍቱ ከተማ ሆራ አርሰዴ ላይ እንደሚከበር ገልጾ በዓሉ በኦሮሞ ህዝቦች ታሪክ ትልቁን ቦታ የሚይዝ መሆኑን አመልክቷል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባህልና የሳይንስ ድርጅት (ዩኔስኮ) ከተመዘገቡ ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ በመሆን የተመዘገበው የገዳ ስርዓት ክዋኔ ታላቅ በዓል መሆኑን በመግለጫው ጠቅሷል።

ከመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተሰጠ የአቋም መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል ።

መደመር ለዕውነት የመቆም ውሳኔ በመሆኑ በተግባር ልናረጋግጠው ይገባናል!

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዘንድሮውን የመስቀል በዓል በድምቀት ያከበርነው ወቅቱ ከምንም ነገር በላይ ተደምረን ለዕውነት የምንቆምበት፣ ደመራም የመደመር በዓል እንደሆነው ሁሉ መደመር አንዱ ከሌላው ጋር የሚያያዝበት እንጂ የሚለያይበትና የሚከፋፈልበት እንዳልሆነ በመረዳት ሁላችንም ለአንዲት አገር ግንባታ በአንድነት እንድንቆም የሚያስገነዝብ ታላቅ መልእክት አንግበን ነው፡፡

አገራችን የጀመረችው የይቅርታ፣የፍቅር፣የመደመር እና የአንድነት ጉዞ ፍሬ ለኢትዮጵያውያን እጅግ አጓጊና ብሩህ ተስፋ ፈንጣቂ ከመሆን ባለፈ የቅርብ ጎረቤትና የሩቅ ወዳጅ አገሮችን ጭምር በትኩረት የሚከታተሉት አብይ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን ታላቅ የለውጥ ንቅናቄና የህዝብ ፍላጎት ይበልጥ አጥርቶ፣ አጠናክሮና አጥልቆ ለመምራት ይቻል ዘንድ የመሪው ድርጅት መስራች አባል ድርጅቶች በጠንካራ ዝግጅት በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡

በድርጅታዊ ጉባኤዎቹ የመክፈቻ ሥነ ስርዓቶች ላይ ከተላለፉት መልእክቶች ለመረዳት እንደሚቻለው ጉባኤዎቹ ከሌሎቹ ጊዜያት በተለየ ሁኔታ የሚመሩ ሲሆን ሲጠናቀቁም በመደመርና በዴሞክራሲያዊ አንድነት መንፈስ ለውጡን በብቃት ለመምራት የሚያስችል ውሳኔ ላይ እንደሚደርሱ፣ ቀጣይ አመራሮቻቻውንም በወጣቱ አዲስ ሃይል ላይ እንደሚያሳርፉ የጠቆሙ ናቸው።

በእነዚሁ መክፈቻ ስነስርአቶች ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው መልዕክቶቻቸውን ያስተላለፉ የእህትና የአጋር ድርጅቶች እንዲሁም የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችም በበኩላቸው አገራችን የተያያዘችው የይቅርታ፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የመደመር ጉዞ አካልና አጋር ሆነው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በድርጅታዊ ጉባኤዎቹ ላይ ከሁሉም አካላት በአንድነት የተላለፉት መልዕክቶች ያረጋገጡልን ዕውነታ አገራችን የተያያዘችውን የፍቅር እና የመደመር ጉዞ በመጻረር በአንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉትን የሁከት እንቅስቃሴዎችን በአንድ ቃል አምርረው ኮንነዋል፤መንግስት የህግ የበላይነት የማስጠበቁን ሃላፊነት በመወጣት ሠላምና ፀጥታን እንዲያስጠብቅ በጥብቅ አሳስበዋል፤ለዚህም ከመንግሥት ጎን ተሰልፈው አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።

የኢፌዴሪ መንግስት ማንም ይሁን ማን በዚህች ሃገር ውስጥ ሲንቀሳቀስ “የህግ የበላይነትን መተላለፍ ቀይ መስመርን እንደ ማለፍ” መሆኑን በተደጋጋሚ ከማስገንዘብ ባለፈ ተግባራዊ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። በዚህ ረገድ ጠንካራ ተሳትፎና ትብብር እያደረገ ላለው፣ እና አንዳች የጸጥታ ችግር ሲፈጠርም ለወገን ደራሽነቱንና የእርቅና አርቆ አሳቢነት እሴቱን በተጨባጭ እየተገበረ ላለው ህዝባችን መንግሥት አድናቆቱን እየገለጸ ምሥጋናውንም ለማቅረብ ይወዳል፡፡

በቀጣዩ ሳምንት በሐዋሳ እንደሚካሄድ የሚጠበቀው የመሪው ድርጅት ጉባኤ በአገራችን የተለኮሰውን የለውጥ ግስጋሴ ወደ ልዩ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው እና በሂደቱም የህዝብን መሰረታዊ ጥያቄዎች በብቃት ለመመለስ የሚያስችለውን ውሳኔዎች እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።

በሌላ በኩል ሃገራችን ኢትዮጵያ ከምትኮራባቸው አያሌ ማህበራዊ ክዋኔዎች መካከል አንዱ የሆነው የኢሬቻ በዓል በፊታችን አሁድ በቢሾፍቱ ከተማ ሆራ አርሰዴ ላይ ይከበራል፡፡

ይህ በዓል በኦሮሞ ህዝቦች ታሪክ ትልቁን ቦታ ከያዘውና በተባበሩት መንግስታት የባህልና የሳይንስ ድርጅት ዩኔስኮ ከማይዳሰሱ የሃገራችን ቅርሶች መካከል አንዱ በመሆን የተመዘገበው የገዳ ስርዓት ክዋኔ አንዱ ማሳያ የሆነ ደማቅ በዓል ነው፡፡

የኦሮሞ ገዳ ስርአት በዓለም ደረጃ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የዴሞክራሲ መሰረትና አገር በቀል የፍትሃዊ አስተዳደር ጥበብ ነፀብራቅ ሆኖ በተጨባጭ እየተሠራበት ያለ ቱባ ሃብታችን ነው፡፡

በመሆኑም በዚህ ወቅትም ሆነ በሌሎች ተመሳሳይ ሃገራዊ ሁነቶች ህዝባችን በብዝሃነት የታጀበውን ህብራዊ ማንነት በማክበርና በመከባበር ህብረ ብሔራዊ አንድነቱን ጠብቆ፣ ልዩነቶቹንም እንደ በረከት በመቀበል በወንድማማችነትና በመደመር ፅኑ ሰንሰለት ተያይዞ ዴሞክራሲያዊ አንድነቱን በድጋሚ ለዓለም ህዝቦች አጉልቶ ማሳየት ይኖርበታል፡፡

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊም ሁለንተናዊውን የለውጥ ጉዞ ከአደናጋሪዎችና በስሜት ከሚገፋፉ ተባባሪዎች ክፋትና ተንኮል ታድጎ ወደ ፊት በማስቀጠል በአዲሱ ዓመት በየተሰማራንበት የሙያ መስክ ሁሉ ውጤታማ አፈፃፀም በማስመዝገብ ለአንዲት ጠንካራ የጋራ አገር ግንባታ የመደመርና ለዕውነት የመቆም ውሳኔዎች በተግባር እንዲያረጋግጥ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል፡፡