የብአዴን ድርጅታዊ ጉባዔ በዲሞክራሲያዊነትና በህዝቡ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ በርካታ ሀሳቦች የተነሱበት መሆኑ ተገለፀ

የብአዴን 12ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ በትላንትናው ውሎው ድርጅቱ ከክልሉ ህዝብ፣ ከአጎራባች ክልሎችና እህት ድርጅቶች ጋር ያለው ዲሞክራሲያዊ ግንኙነት ጥያቄ የተስተናገደበት መሆኑ ተገለፀ።

የጉባዔው ቃል አቃባይ አቶ ምግባሩ ከበደ ውሎ በተመለከተ በሰጡት መግለጫ፥ ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች በዛሬው ውሎ መነሳተቸው ተናግረዋል።

እነዚህም የድርጀቱ ፓለቲካ ስራና አደረጃጀት፣ የዲሞክራሲ ግንባታ ከእነ አተገባበሩ እንዲሁም የክልሉ ህዝብ የልማት ጥያቄዎች ካገኙት ምላሽ ጋር የተነሱ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የጉባዔው ተሳታፊዎች፥ የድርጅቱ የአባላት ምልመላ፣ የፓለቲካ ብቃት ላይ ጥያቄዎችን ማስታቸውንም ነው የገለፁት።

የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን በተመለከተ የድርጅቱ አመራሮች ከአማራ ህዝብ ጋር ያላቸው ዲሞክራሲያዊ ግንኙነትም ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል ይጠቀሳል ብለዋል።

በድርጅቱ መሪዎችና በህዝቡ፣ በድርጅቱና በአጎራባች ክልሎች፣ እህትና አጋር ድርጅቶች ጋር ስላለው ግንኙነትና ዲሞክራሲያዊነት ላይ ጥያቄዎች መነሳቸውን አብራርተዋል።

እንዲሁም ከልማት ጋር በተያያዘ ጉባዔተኞቹ የአማራ ህዝብ ባለው ፀጋና የተፈጥሮ ሀብት አየለማ ስለመሆኑ ጥያቄዎችን ማቅረባቸው ታውቋል።

የክልሉ ፈተና የሆነው የስራ ፈጠራ፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ላይም ጠንካር ሀሳቦች በጉባዔው ላይ ተዘንዝረዋል ተብሏል።

በተጨማሪም በአማራ ክልልና በሌሎች ክልሎች፣ በክልሉ ባሉ አካባቢዎች መካከል ስላለው የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይም ጥያቄዎችና ሀሳቦች ጉባዔተኞቹ ማንሳታቸው ተነግሯል።

ጉባዔው በትላንትና ውሎው የፌዴራል መንግስት ለክልሎች በሚደለድላቸው የልማት ስራዎች ላይ በተሳታፊዎች በኩል እንደተነሳ ተጠቁሟል።

ጉባዔው በዛሬው ውሎ በጉባዔው ሪፓርት ላይ ሲመክር ይውላል ተብሏል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)