ህወሃት የ12 ነባር አመራሮችን ማሰናበቱን አስታወቀ

ህወሃት እያካሄደ  ባለው ድርጅታዊ ጉባዔ 12  ነባር  አመራሮችን ማሰናበቱን አስታውቋል ።

በተጨማሪም በድርጅታዊ ጉባዔው በትናንት  ውሎው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ያካሄደ ሲሆን፥ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ቁጥርም ከ45 ወደ 55 ከፍ እንዲል ወስኗል።

በዚህም መሠረት 65 እጩዎች ለማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት የቀረቡ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ የ55 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በተካሄደው ድምጽ የመሥጠት ሥርዓት ተመርጠዋል።

ለማዕከላዊ ኮሚቴ ከተመረጡት 55 ውስጥ 45ቱ ለኢህአዴግ ምክር ቤት አባልነት የሚቀርቡ እንደሆነ ተገልጿል ።

ለማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት የተመረጡት ዝርዝርም በዛሬው ዕለት ይፋ እንደሚደረግ ታውቋል።

ድርጅታዊ ጉባዔው በዛሬ ውሎው 12 ነባር አመራሮችንም በክብር አሰናብቷል።

የህወሃት ድርጅታዊ ጉባዔ በዛሬው ዕለት  የድርጅቱን ሊቀ መንበር እና ምክትል ሊቀመንበር ምርጫን እንዲሁም የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫን እንደሚያካሄድ ይጠበቃል።

በተጨማሪም የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን አባላት ምርጫ በማካሄድ አጠቃላይ ጉባኤው ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ህወሓት እየተካሄደ ባለው ድርጅታዊ ጉባኤው ከአመራርነት እንዲሰናበቱ ያደረጋቸው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ዝርዝር የሚከተሉት ናቸው ።

በዚህም መሰረት፦

1 አቶ አባይ ወልዱ

2 ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ

3 አቶ ገብረመስቀል ታረቀኝ

4 አቶ ሚካኤል አብረሃ

5 አቶ ጎበዛይ ወልደአረጋይ

6 አቶ ኢሳያስ ወልደጊዮርጊስ

7 አቶ ነጋ በረኸ

8 አቶ ተወልደብርሃን ተስፋዓለም

9 አቶ ማሞ ገብረእግዚአብሄር

10 አቶ ጎይቶም ይብራህ

11 አቶ ሀይሌ አሰፈሃ

12 አቶ ኪሮስ ቢተው ከድርጅቱ በክብር ተሰናብተዋል።