በ11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ለሚተላለፉ ውሳኔዎች ተግባራዊነት ድጋፍ እንደሚያደርጉ አጋር ድርጅቶች ገለጹ

በ11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ለሚተላለፉ ውሳኔዎች ተግባራዊነት ድጋፍ እንደሚያደርጉ የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች ገለጹ።

11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ በዛሬው እለት በሃዋሳ ከተማ በይፋ የተከፈተ ሲሆን በመክፈቻው ላይ ንግግር ያደረጉት የአጋር ድርጅት ተወካዮች በጉባኤው ላይ ለሚተላለፉ ውሳኔዎች እና ለሚቀመጡ አቅጣጫዎች ተፈጻሚነት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ተወካይ ባስተላለፉት መልዕክት ኢህአዴግ ለህዝቦች ነጻነትና እኩልነት ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈሉን አንስተዋል።

ኢህአዴግ ባለፉት አመታት በርካታ ስኬትና ድል አስመዝግቧል ያሉት ተወካዩ፥ ከዚህ ባሻገር ግን ያልተመለሱ ጥያቄዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም የህዝቦችን ሰብዓዊ መብት ማስከበር፣ ያልተመሰሉ ጥያቄዎችን መመለስና የሚስተዋሉ ግጭቶችን ማስወገድ ይገባል ብለዋል።

የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ተወካይ በበኩላቸው ኢህአዴግ መሰረታዊ ለውጥ በማምጣት የህዝቦችን እና የብሄር ብሄረሰቦችን መብት ማስከበር መቻሉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ተወካይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ለተመዘገቡ ለውጦችና ስኬቶች የላቀ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል።

በ11ኛው ጉባኤ ላይም ሃገሪቱን ወደ ፊት የሚያራምዱና የህዝቡን ጥያቄ የሚመልሱ ውሳኔዎች ይተላለፋል ብለው እንደሚጠብቁም ጠቅሰዋል።

ኢህአዴግ ህዝባዊ ድርጅት መሆኑን ያነሱት ደግሞ የሃረሪ ብሄራዊ ሊግ ተወካይ ናቸው።

ተወካዩ በጉባኤው ለውጥ አደናቃፊ ሂደቶችን በመቀልበስ አሁን የታየውን ሃገራዊ ለውጥ በህዝቡ ባለቤትነት ወደማይቀለበስበት ደረጃ ማድረስ የሚያስችል ውሳኔ እንደሚተላለፍ እምነታቸው መሆኑንም አንስተዋል።

የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ተወካይ በበኩላቸው ኢህአዴግ ብሄሮች ማንነታቸውን እንዲያስከብሩና በራሳቸው ጉዳይ ራሳቸው እንዲወስኑ ያስቻለ ድርጅት መሆኑን ነው የተናገሩት።

በተለይም ደግሞ በጋምቤላ ክልል ለተመዘገቡ ለውጦች ኢህአዴግ ከፍ ያለ ሚና ተወጥቷልም ነው ያሉት።

አጋር ድርጅቶቹ በዚህ ጉባኤ ላይ የታየውን ጅምር ለውጥ የሚያረጋግጡ ውሳኔዎች እንደሚተላለፍ እምነታቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም ሃገሪቱን እና ለውጡን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ብለው እንደሚያምኑም አስረድተዋል።

ፓርቲዎቻቸውም ከአጋርነት አልፈው በሃገራዊ ጉዳይ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሚሆኑበት ውሳኔ በዚህ ጉባኤ ላይ ይተላለፋል ብለው እንደሚያምኑም አንስተዋል። (ኤፍ ቢ ሲ)