የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አዲስ የመዋቅር ማሻሻያና ድልድል ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥራውን  ውጤታማ  ሊያደርግ  የሚያስችል አዲስ የመዋቅር ማሻሻያና የሠራተኛ ድልድል ሊያካሄድ መሆኑን አስታወቀ ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ አቶ መለስ ዓለም በዛሬ ዕለት በሠጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ሚኒስቴሩ ቀደም ሲል የነበረውን መዋቅር ፈትሾ ጠንካራና ደካማ ጎኖቹን ለይቶ አዲስ መዋቅር በመሥራት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ሚኒስቴሩ የሰው ሃብት ስምሪቱን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል አዲስ የሠራተኛ ድልድል በዋናው መሥሪያ ቤትና በመላው ዓለም በሚገኙ ሚሲዮኖች በቅርቡ እንደሚካሄድ አቶ መለስ ገልጸዋል፡፡

የሰው ኃይል ምደባው ሌሎች መመዘኛዎች እንዳሉ ሆነው ሥራና ሠራተኛን ሙያዊ ክህሎትን እንዲሁም በአጠቃላይ ፕሮፌሽናሊዝምን መሠረት ያደረገ እንዲሆን ይደረጋል ብለዋልቃል አቀባዩ  በመግለጫቸው ፡፡

የማሻሻያ ጥናቱ ላይ ሠራተኛው  ውይይት እንዲያደርግበት መደረጉንና  የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ሚኒስቴር ግምገማ ተካሄዶበት በጠቅላይ ሚኒስትሩ መጽደቁን ነው የተገለጸው፡፡

የሪፎርሙ ዓላማም መሥሪያ ቤቱ የአገሪቱን የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ሥራ እንዲያሳካ  ለማድረግ መሆኑን  ቃል አቀባዩ ተናግረዋል ።

ሚኒስቴሩ ለወደፊቱ ለሚጠብቁት የዘመኑ ዕድሎችና ፈተናዎች የሚመጥን ተቋም እንዲሆን በማድረግ ለብሔራዊ ጥቅም የሚቆም የአገር ፍቅርና ክህሎት፣ ዕውቀት ያለው ዲፕሎማት ማፍራት ነው ተብሏል፡፡