11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ በ10ኛው የድርጅታዊ ጉባኤ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች አፈጻጻም ላይ ተወያየ

11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ በ10ኛው የድርጅታዊ ጉባኤ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች አፈጻጻም እንዲሁም በአገራዊ ለውጥ ላይ ውይይት አድርጓል ።    

የ11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ቃል አቀባይ አቶ ፍቃዱ ተሰማ  በዛሬው ዕለት በሠጡት መግለጫ  ጉባኤው  በጠዋት ውሎው  የቡድን  ውይይት ያደረገ ሲሆን ከሰዓት  በኋላ  በተያዙ የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ  በጋራ  ሰፊ ውይይት  ተደርጓል ብለዋል  ።

በወቅታዊ አገራዊ  ሁኔታና ለውጡን በብቃት መምራትን በተመለከተ ሰፊ ውይይት ያካሄደው  ጉባኤው ድርጅቱ  የአመራር ለውጥን  ካደረገ በኋላ በአገሪቱ  ለውጦች መምጣታቸውን  በጉባኤው ተሳታፊዎች በሰፊው ተነስቷል ።

ባለፉት ስድስት ወራት ጠቅላይ  ሚንስትር  ዶክተር አብይ ከተለያዩ ህዝቦች ውይይት  በማድረጋቸው በአገሪቷ አንጻራዊ  ሰላምና መረጋጋት መምጣቱንም በጉባኤው  መገለጹን  አቶ ፍቃዱ  ተናግረዋል ።

በአገሪቱ  የፖለቲካ  ምህዳሩን  ለማስፋት በተደረገው  ጥረትም በውጪ አገራት የሚገኙ እንዲሁም  የታጠቁ በርካታ  የፖለቲካ ድርጅቶች  ሰላማዊ ትግል  ለማድረግ ወደ አገር ውስጥ  መግባታቸው ትልቅ ውጤት መሆኑ በጉባኤው  ስለመነሳቱ ቃል አቀባዩ አመልክተዋል ።

በማረሚያ ቤቶች ይፈጸሙ የነበሩ  የተለያዩ ኢ-ሰብዓዊ የመብት ጥሰቶችም ላይ የተወሰዱት እርምጃዎች አመርቂ ውጤት  ማስመዝገብ  መቻሉንም  የጉባኤው ተሳታፊዎች  በሰፊው መግለጻቸውንም  ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል ።

በውጭ  የዲፕሎማሲያዊ ሥራን  በተመለከተ  ኢትዮጵያ  ከጎረቤት አገራትና  በዓለም አቀፍ  መድረኮች  ተገቢውን  የዲፕሎማሲያዊ  ግንኙነቶች  በመፍጠር ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገብ  መቻሏን  በውይይቱ  መታየቱን ቃል አቀባዩ አንስተዋል ።

በተለይም  ሁለት  አሥርት ዓመታትን  ባስቆጠረው የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ማጣት  ችግርን   በመፍታት  ህዝቦቹን  ዳግም  ወደ  ሰላም  መምጣት  ተችሏል ይህም በጉባኤው በስኬትነት  የተጠቀሰ  ተግባር መሆኑን ተገልጿል ብለዋል ።

በመገናኛ ብዙሃን  ነጻነትን ለማስጠበቅ  በተደረገው ጥረት  በውጭ  የሚገኙ  እንደ  ኢሳትና ኦኤም ኤን የመሳሳሉት ሚዲያዎች   ወደ አገር  ውስጥ ገብተው በነጻነት እንዲሠሩ  ከመደረጉም በላይ  ከ250 በላይ  የሚሆኑ ድረገጾችና ብሎጎች  መልሰው  እንዲሠሩ በማድረግ  የፕሬስ ነጻነቱን  በማስከበር ረገድ ውጤት መገኘቱን በወይይቱ መጠቆሙን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል ።

በአገሪቱ   ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ሪፎርሞች  እንደሚያስፈልጉ በጉባኤው  ውይይት እየተደረገበት የሚገኝ ሲሆን ከህዝቡ  ፍላጎት ጋር የሚጣጣም የመንግሥት አገልግሎት  ተቃማትም ሊኖሩ  እንደሚገባ  አጽዕኖት  በመሥጠት ውይይት መደረጉን ቃልአቀባዩ ገልጸዋል ።

11ኛው  የኢህአዴግ ጉባኤ በወይይቱም  የተደራጀ  ሌብነትንና ዘረፋን ፣ ግለኝነትና በሥራ ላይ ውጤት አልባነት እንዲሁም ሥርዓት አልበኝትን የማይታለፉ ቀይ መስመሮች መሆናቸውንም በግልጽ በመድረክ ያስቀመጣቸው ነጥቦች መሆናቸውን ቃልአቀባዩ አስረድተዋል ።

አገራዊ መግባባትን  ለመፍጠርም በተደረገው ጥረትም  በስደት  የነበረውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሲኖዶስ  እንዲመለስና  በሙስሊም  መፍትሄ አፈላላጊና በመጅሊሱ  በኩል መግባባት  እንዲፈጠር  ተገቢው  ሥራዎች  መከናወናቸው በጉባኤው ስለመገለጹ  ቃል አቀባዩ  ጠቁመዋል ።

ከኢኮኖሚ አኳያም በመንግሥት  ተይዘው የነበሩ  ሃብቶችን አቅም ያላቸው  አገር ወዳድ ባለሃብቶች ድርሻ  እንዲኖራቸው  የሚካሄዱትም ሥራዎች መጀመራቸው  በአወናታዊ መልኩ በጉባኤው መታየቱን ቃል አቀባዩ  አንስተዋል ።

የ11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ  አገራዊ  ለውጡን ለማስቀጠል  በሚያስችሉ አጀንዳዎች  ላይ ሰፊ ውይይት እያደረገ  ሲሆን   በነገው ዕለት   የድርጅቱ  መሪዎችን  በመምረጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል ።