11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ባለሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ

ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።

.አሁን ላይ ሃገሪቱ ወደ ለውጥ ምዕራፍ ገብታለች፤ የጉባኤው ተሳታፊዎችም ለውጡ እንዳይቀለበስ ለማድረግና ለማስቀጠል ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው በመግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡

.ዴሞክራሲን በማስፋትና ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፤ ከዚህ አንጻርም የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲጠናከር ለመስራት ቃል ገብተዋል፡፡

.በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች የዜጎች መብት ጥሰት የሚስተዋል በመሆኑ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ የማንነት ጥያቄዎችም በህግ አግባብ እንዲፈቱ ማድረግ፤

.ምርታማነትን በማሳደግና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር በማድረግ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ለመፍጠር ጠንክሮ መስራት፤

.ከጎረቤት ሃገራት ጋር የሚኖር ግንኙነት መልካም ጉርብትናንን በሚያጠናክር መልኩ ሆኖ ይቀጥላል።

.የህግ የበላይነት እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ማድረግ፤

.የተሃድሶ እንቅስቃሴውን አጠናክሮ ማስቀጠልና ሀገራዊ ለውጡን ወደፊት ማስኬድ መቻል፤

ከአቋም መግለጫው ባለፈም ጉባኤው የታየው ሃገራዊ ለውጥ ብሄራዊ መግባባትን ከመፍጠር አኳያ ላቅ ያለ ሚና እንዳለው ገምግሟል።

ከዚህ አንጻርም ለውጡን ህዝባዊ፣ ህግ መንግስታዊና ድርጅታዊ በማድረግ ለውጡ እንዳይቀለበስ ጉባኤተኞቹ የድርሻቸውን ለመወጣት ቃል ገብተዋል።

የዜጎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመስራት መብት እንዲከበርና ብሄራዊ ማንነትና ሃገራዊ አንድነት እንዲጠናከር አበክሮ መስራትም በጉባኤተኞቹ ስምምነት የተደረሰበት ጉዳይ ነው።

በኢኮኖሚው የዜጎችን በተለይም የወጣቶች እና ሴቶችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ እንደሚሰሩም ጉባኤተኞቹ ቃል ገብተዋል።

በዲፕሎማሲው መስክ በተለይም የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራ ሆኖም ተገምግሟል።

ስርዓት አልበኝትን በማስወገድና ሰላምን በማስፈን የህግ የበላይነትን ማረጋገጥና ለህግ የበላይነት መከበርና ለሰላም መስፈን የሚተጋ ዜጋን መፍጠርም በጉባኤው አጽንኦት ተሰጥቶታል።

መላው ህብረተሰብም ለውጡ እንዳይቀለበስና እንዲቀጥል የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ ቀርቧል።

ከዚህ ባለፈም ወጣቶችና ሴቶች ለውጡ እንዲጠናከርና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጥሪ ቀርቧል።

ምሁራንም በእውቀታቸው ለሃገር የሚበጁ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማድረግ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባልም ነው የተባለው።

አጋር ድርጅቶችም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሳተፍበት አንድ ሃገራዊ ፓርቲ ለመመስረት የተጀመረውን ጥረት በማገዝ ለጥረቱ ስኬት ድጋፍ ያደርጉ ዘንድም ኢህአዴግ ጥሪውን አቅርቧል።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለተጀመረው ሃገራዊ ለውጥ ስኬት ወቅቱ የሚጠይቀውን የአንድነት መንፈስ በመላበስ ገንቢ ሚና ሊጫወቱ ይገባል ተብሏል።

የፀጥታ አካላትም ፀጥታን የማስከበር ህገ መንግስታዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል።