አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል ለሚወጡ አቅጣጫዎች ተግባራዊነት በጋራ እንረባረብ- መንግስት

አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል የሚወጡ አቅጣጫዎች ተግባራዊነት ሁሉም በጋራ እንድረባረብ መንግስት ጥሪ አቀረበ፡፡

የመሪ ድርጅቱ -ኢህአዴግ- አባል ድርጅቶች ጠቅላላ ጉባኤዎቻቸውን ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ፣ "አገራዊ አንድነት ለሁለንተናዊ ብልጽግና" በሚል መሪ ቃል በሃዋሳ ከተማ የተካሄደው 11ኛው የግንባሩ ድርጅታዊ ጉባዔ በብዙ መልኩ ሲታይ ታሪካዊ ሊባል የሚችል መሆኑን የኢፌዲሪ መንግስት ኮሙኒኬሽን ባወጣው ሳምንታዊ መግለጫ አመላክቷል፡፡

አገሪቱ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መስኮች በከፍተኛ የለውጥ ሂደት ውስጥ በምትገኝበት እና በእስካሁኑ ሂደትም ጉልህ፣ መሰረታዊ እና ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ ባሉበት ወቅት ላይ የተካሄደ በመሆኑ ጉባኤው ታሪካዊ ነው ብሏል።

የተፈጠረው ፖለቲካዊ መረጋጋት አደጋ ላይ ወድቆ የነበረውን የአገራችንን ህልውና የታደገ በመሆኑ ከምንም በላይ የለውጡ ታላቅ ስኬት ተደርጎ መወሰድ ያለበት ጉዳይ እንደሆነም መግለጫው አንስተዋል፡፡

የተጀመረውን ተስፋ ሰጪ ለውጥ የሚያደናቅፉና አቅጣጫ የሚያስቱ ተግባራትን በጋራ ሆኖ በመግታት ሁሉም ህብረተሰብ ለለውጥ ሂደቱ ያላቸውን አጋርነት በተግባር የሚያረጋግጡበት ወቅት መሆኑንም መገንዘብ እንደሚገባ ለጣቢያችን በላከው መግለጫ አሳስቧል፡፡

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

 

ከኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተሰጠ ሳምንታዊ የአቋም መግለጫ፡

አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል ለሚወጡ አቅጣጫዎች ተግባራዊነት በጋራ እንረባረብ!

የመሪ ድርጅቱ -ኢህአዴግ- አባል ድርጅቶች ጠቅላላ ጉባኤዎቻቸውን ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ፣ "አገራዊ አንድነት ለሁለንተናዊ ብልጽግና" በሚል መሪ ቃል በሃዋሳ ከተማ የተካሄደው 11ኛው የግንባሩ ድርጅታዊ ጉባዔ በብዙ መልኩ ሲታይ ታሪካዊ ሊባል የሚችል መሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

አገሪቱ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መስኮች በከፍተኛ የለውጥ ሂደት ውስጥ በምትገኝበት እና በእስካሁኑ ሂደትም ጉልህ፣ መሰረታዊ እና ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ ባሉበት ወቅት ላይ የተካሄደ በመሆኑ ጉባኤው ታሪካዊ ነው ተብሏል።

በተለይም አሁን የተፈጠረው ፖለቲካዊ መረጋጋት አደጋ ላይ ወድቆ የነበረውን የአገራችንን ህልውና የታደገ በመሆኑ ከምንም በላይ የለውጡ ታላቅ ስኬት ተደርጎ መወሰድ ያለበት አብይ ጉዳይ ነው።

የፖለቲካ እና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት መንግሥት በወሰዳቸው አበይት የለውጥ እርምጃዎች የተነሳ ከማረሚያ ቤት የወጡ፣  ከትጥቅ ትግል ወደ ሰላማዊ ትግል የተመለሱ፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ በህጋዊነት ከሚንቀሳቀሱት በተጨማሪ በውጭ አገራት ሆነው የተቃውሞ ፖለቲካ ሲያራምዱ የቆዩ ሃይሎች ሁሉ በጉባኤዎቹ የመክፈቻ ሥነ ስርዓት ላይ እየተገኙ ሃሳባቸውን ሲያንጸባርቁና ምክራቸውን በይፋ ሲለግሱ የታዩበት ሂደት በእርግጥም የታላቅ ክንውን ውጤት መሆኑ አይዘነጋም ይላል መግለጫው።

ጉባኤዎቹ በሚካሄዱበት ወቅት ሕዝብ ያለምንም መሸማቀቅ የመሰለውን ሃሳብ እየገለጸ ሚዲያዎቻችን የተለያዩ ሃሳቦችን በነጻነት ሲያንሸራሽሩ ማዬት ተስፋ ሰጪ የለውጥ ክስተት ነው ተብሏል።

በውጭ አገራት ሆነው በሚያራምዱዋቸው የተለዩ ሃሳቦች የተነሳ ተዘግተው የነበሩ ሚዲያዎች እና ድረገፆች ዛሬ በመሪ ድርጅቱ እና በመንግሥት የስብሰባ አዳራሾች እየተገኙ ታላላቅ አገራዊ ጉዳዮችን በነጻነት እየዘገቡ ያሉበትን ሁኔታ በአጽንኦት መመልከትም የጉባዔውን ታሪካዊነት ለመመስከር የሚያግዝ መሆኑ ተመላክቷል።

የፖለቲካ ምህዳሩን በማጥበብ ረገድ የራሳቸውን ሚና ሲጫወቱ የነበሩ ህግጋትን በሕዝቡ፣ በምሁራን እና በባለሙያዎች አስተያየት እና ተሳትፎ ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት፣ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግር የነበረባቸውን የጸጥታ እና የህግ አስከባሪ ተቋማትን የህዝብ አገልጋይ ለማድረግ ከአመራር እስከ አደረጃጀት እና አሰራር ማሻሻያ የዘለቀ የለውጥ ሥራ እየተካሄደ ባለበት በዚህ ወቅት የተካሄደ ጉባዔ እንደመሆኑ መጠን ታሪካዊነቱን የጎላ ያደርገዋል።

ተወደደም፣ ተጠላም  የአገራችን መጻኢ ዕድል በጎም ይሁን መጥፎ የሚወሰነው አሁን ባለው ትውልድ መሆኑን በጥልቀት መገንዘብ ያሻል። በመሆኑም የፖለቲካ ልሂቃኖቻችን የብሔር እና የፖለቲካ ልዩነቶችን መሰረት አድርገው ከመቆራቆስ ወጥተው ጊዜያቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ ሃብትና ጉልበታቸውን አስተባብረው ለሰላም፣ ለፍትህ፣ ለብልጽግና ለእኩልነት እና ለአንድነት በጋራ ለመስራት ከዚህ የተሻለ ዕድል አይኖራቸውም።

የተጀመረውን ተስፋ ሰጪ ለውጥ የሚያደናቅፉና አቅጣጫ የሚያስቱ ተግባራትን በጋራ ሆኖ በመግታት ለለውጥ ሂደቱ ያላቸውን አጋርነት በተግባር የሚያረጋግጡበት ወቅት መሆኑንም መገንዘብ ይገባል ነው የተባለው።

ይህ አጓጊ እድል የተገኘው በዋዛ ሳይሆን በከፍተኛ መስዋዕትነት እንደመሆኑ መጠን ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት በላይ ብዝሃነታችንን ያከበረ አገራዊ አንድነትን በማስቀደም፣ የአንዳችን ጉዳት የሌላችን ጉዳት መሆኑን አምኖ በመቀበል የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት የሁላችንንም አገራዊ ኃላፊነት መወጣት የሚጠይቅ ነው።

በመሆኑም በአገራችን እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ለማስቀጠል ሲባል መሪው ድርጅት በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ለሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች እና ለሚያስቀምጣቸው አቅጣጫዎች ተግባራዊነት መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች በጋራ እንዲረባረቡ የኢፌዴሪ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል፡፡