ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢን በማስተሳሰር ረገድ ጉልህ ሚና መጫወታቸው ተገለፀ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነት እንዲፈጠር ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን የሁለት አፍሪካ አገራት ገዥ ፓርቲዎች ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሃላፊነት በመጡ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወደ ጎረቤት ሀገራት ጅቡቲ፣ ኬኒያ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያና ኤርትራ በማቅናት ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር ምጣኔ ኃብትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ተባብራ ለመስራት የሚያስችላትን ስምምነት ፈርመዋል።

በተለይ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የዘለቀውን የኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላም ችግር በመፍታት ረገድ የተጫወቱት ሚና በበርካቶች ዘንድ አድናቆት አትርፎላቸዋል።

ሳውዲ አረቢያና የተባባሩት አረብ ኢምሬትስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድና ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ችግሩን ለመፍታት ለወሰዱት ቆራጥ አርምጃና በጎ ተግባር በይፋ እውቅና መስጠታቸውን ለአብነት ማንሳት ይቻላል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ደቡብ አፍሪካን እየመራ ያለው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረንስ (ኤ ኤን ሲ) እና የኬኒያውን ጁበሌ ፓርቲ አመራሮች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ጥቂት ወራቶች የከወኗቸውን እነዚህን ጥረቶች አድንቀዋል።

የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረንስ  ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ፕሮፌሰር ኤቅባህ ጃህዝዋህይ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ያላት የፖለቲካና የምጣኔ ኃብታዊ መልካም ሁኔታ እንዲሁም ወጣት የሰው ኃይል ለቀጠናው ልማት ትልቅ ደርሻ እንዲኖራት እድል ፈጥሮላታል።

የቀጠናው አገራት ከኢትዮጵያ ጋር ለመተሳሰር ከፍተኛ ፈላጎት አላቸው ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ያለውን ችግር በመፍታት ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚደነቅ እርምጃ ወስደዋል ያሉት ፕሮፌሰር ኤቅባህ ጃህዝዋህይ፤ መሪዎቹ ላከናወኑት ተግባር  ፓርቲያቸው እንኳን ደስ አላቸሁ ማለቱን ገልጸዋል።

ሁለቱ አገራት በጋራ በመሆን በአህጉሩ ተጽእኖ ፈጣሪ አገራት እንዲሁም ለዓለም አዲስ የሰላም ሂደት ምሳሌዎች መሆን ይችላሉ ነው ያሉት።

የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረንስ ከኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር  /ኢህአዴግ/ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር  እንደሚሰራም አክለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እያከናወኑት ባለው ተግባር “እንደ አገር ተደስተናል” ያሉት ደግሞ በኬኒያ ጁበሌ ፓርቲ የቀጠና ጉዳዮች ዳይሬክተሩ አብርሃም ሊሞ ናቸው።

በኢትዮጵያ የተፈጠረው ውስጣዊ ሰላም አገሪቱ ከቀጠናው አገራት ጋር በተለያዩ ልማቶች ለመተሳሰር እንድትሰራ ጉልህ ሚና መጫወቱንም አክለዋል።

የደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረንስ ፓርቲ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1912 ተመስርቶ ከ1994 ጀምሮ አገሪቱን እየመራ ይገኛል።

የኬንያው ጁበሌ በበኩሉ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2016 በኬኒያ የሚንቀሳቀሱ ስምንት የተለያዩ ፓርቲዎች በጋራ ጥምረት የመሰረቱት ነው።