ምክር ቤቱ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ለማሳደግ በመረጃ ቴክኖሎጂ የበለጸገ አሰራር ሊተገብር ነው

የህብረተሰቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በመረጃ ቴክኖሎጂ የበለጸጉ አሰራሮችን ሊተገብር መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ።

የህብረተሰቡን ተሳትፎና ፍላጎት ለማርካት ምክር ቤቱ መዋቅራዊ ለውጥና ማሻሻያ የሚያደርግባቸው አሰርሮችም በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚሆኑ ተገልጿል።

ምክር ቤቱ ዛሬ የሚጀምረውን የፌዴሬሽንና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች 5ኛ ዓመት 4ኛ የስራ ዘመን የጋራ መክፈቻ መርሃ ግብር በተመለከተ ትላንትና መግለጫ ሰጥቷል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የምክር ቤት አባላትና የወከሉትን ኅብረተሰብ እርስ በርስ በቀላሉ መገናኘት የሚችሉበት አሰራር ተዘርግቷል።

ህብረተሰቡና ተገልጋዩ ባለበት ቦታ ሆኖ በቀላሉ መረጃዎችን ማግኘት፣ መጠየቅና አስተያየት መስጠት የሚችልበት ነፃ የስልክ ጥሪ፣ የሞባይል መተግበሪያ (Application) እና ሌሎችም በቴክኖሎጂ የበለጸጉ መሳሪያዎች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ አመልክተዋል።

አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች በኅብረተሰቡ ዘንድ በቀላሉ ስለማይገኙና ህዝቡም ስለማያውቃቸው ሰፊ የመልካም አስተዳደር ችግር ሲያደርሱ መቆየታቸውን አስታውሰው ከህግ ማርቀቅ ጀምሮ ህጉ ተግባራዊ እስከሚደረግ ባለው ሂደት የኅብረተሰቡ ተሳትፎ አነስተኛ እንደነበር በጥናት መለየቱን ገልጸዋል።

በቅርቡ ተግባራዊ የሚደረገው የሞባይል መተግበሪያ ተገቢ ምላሽ እንደሚሰጥ እምነት እንዳላቸው አፈ-ጉባዔዋ ተናግረዋል።

ማንኛውንም ጥቆማ ለመስጠት ኅብረተሰቡ ማመልከቻ ማስገባት ሳያስፈልገው በተወካዮቻቸው አማካኝነት ማድረስ የሚችሉበት የጥቆማ አስተዳደር ስርዓት መዘርጋቱንም ጠቁመዋል።

ዜጎች ተወካያቸውን ባሉበት ቦታ ሆነው በቀጥታ ማግኘት የሚችሉበት ቴሌ ፕሬዘንስ (Tele Presence) ቴክኖሎጂ ስራ ላይ እንደሚውልም ገልጸዋል።

በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ተደራሽ የሚደረገው መረጃ በቂ ባለመሆኑ ምክር ቤቱ የራሱ የመገናኛ ብዙሃን ተቋም እንደሚኖረውም አመልክተዋል።

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀም ባለፈ የክትትልና ድጋፍ አግባቡን ግልጽነትና ተጠያቂነት በሰፈነበት መንገድ ለማከናወን ማሻሻያ ተደርጎበታል።

ምቹ የስራ ሁኔታ መፍጠር እንዲሁም የኦዲት ስርዓቱን ማሻሻል ምክር ቤቱ ተግባራዊ የሚያደርጋቸውና በትኩረት የሚሰራባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አብራርተዋል።

ባለፉት አራት ወራት የክረምቱን ወቅት ጨምሮ እነዚህን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና የአሰራር ማሻሻያዎች ተግባራዊ ለማድረግ አብዛኛው የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

”የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች የኅብረተሰቡን ፍላጎት የሚያረኩና ለጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ እንዲሆኑ የበጀት ዓመቱ ቁልፍ ስራችን ናቸው” ብለዋል።

የምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት ስነ ምግባር ደንብ እነዚህን ማሻሻያዎች በአግባቡ መተግበር በሚያስችል መልኩ የሚሻሻል መሆኑንም  አስረድተዋል። (ኢዜአ)