አጋር ድርጅቶች ግንባሩን እንዲቀላቀሉ የተቀመጠው አቅጣጫ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ያግዛል- አቶ አደም ፋራህ

የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች ግንባሩን እንዲቀላቀሉ የተቀመጠው አቅጣጫ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚረዳ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ፡፡

በጉባኤው ላይ የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች ግንባሩን እንዲቀላቀሉ ለማስቻል እና ኢህአዴግ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ድርጅት እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል አቅጣጫ መቀመጡ ደግሞ የሶማሌ ክልል ህዝቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ሰላምና ጸጥታ በአስተማማኝ ሁኔታ ተረጋግጦ ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል የሚያስችል ቁመና ለመያዝ የክልሉ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ህዝቡ ከመንግስት ጎን ሊቆም እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ከመስከረም 23 እስከ 25/2011 ዓም የተካሄደው 11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፎና አቅጣጫዎችን አስቀምጦ መጠናቀቁ የሚታወስ ሲሆን ከውሳኔዎቹ መካከል ደግሞ ለውጡን ማስቀጠል፣ ስርዓት አልበኝነትን አለመታገስና የተደራጀ ሌብነትና ዘረፋን መከላከል የሚሉት ይገኙበታል፡፡

እነዚህ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ለሀገር የሚበጁ በመሆናቸው በውሳኔዎቹ ደስተኞች መሆናቸውን ዋልታ ያነጋገርናቸው የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡