‘ኦነግ ወደ ሀገር የገባው ትጥቅ ፈትቶ ነው ካልሆነ ግን መንግስት ትጥቅ የማስፈታቱን ስራ ይሰራል’’ አቶ ካሳሁን ጎፌ

ኦነግ ወደ ሀገር የገባው ትጥቅ ፈትቶ ነው አሁንም ቢሆን የቀረውን ትጥቅ መፍታት አለበት፤ ካልሆነ ግን መንግስት የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅና ህገመንግስታዊ ስርዐቱን ለማስጠበቅ ሲል ትጥቅ የማስፈታቱን ስራ ይሰራል ሲሉ የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ ገልጸዋል፡፡

ከሰሞኑ የኦነግ አመራር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ከመንግስት ጋር ትጥቅ ለመፍታት አልተደራደርንም፤ ትጥቅ የሚፈታም የሚያስፈታም የለም ማለታቸውን ተከትሎ ዛሬ የኢፌዲሪ ////ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ በጉዳዩ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ባደረገው የሰላም ጥሪ መሰረት በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶችና የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ሀይሎች ወደሀገር መግባታቸውን ያስታወሱት አቶ ካሳሁን ኦነግም ወደሀገር ሲገባ 1300 ያህል ጦሩን ትጥቅ አስፈትቶ መግባቱንና ጦሩም በአሁኑ ሰአት በአርዳይታ ማሰልጠኛ ስልጠና እየተከታተለ ነው ብለዋል፡፡

ኦነግ በአስመራ በተደረጉ ሶስት ድርድሮች በሰላማዊ መንገድ ወደ ሀገር ገብቶ ለመፎካከር መስማማቱ የሚታወቅ ነው፤ ለዚህም ወደሀገር ሲገባ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል ያሉት አቶ ካሳሁን በድርድሩ ወቅት ትጥቅ የመፍታት ጉዳይ ያልተነሳው የመደራደሪያ ጉዳይ ስላልሆነ ነው ብለዋል፡፡

ሰላማዊ ትግል የሚደረገው በሀሳብ እንጅ በአፈሙዝ ስላልሆነ ትጥቅ የመፍታትን ጉዳይ ለድርድር የማናቀርበውና ቀይ መስመር ነው ሲሉ አቶ ካሳሁን በመግለጫቸው ተናግረዋል፡፡

ስለሆነም ኦነግ አቋሙን እንደገና በመፈተሽ ትጥቁን እንዲፈታ መንግስት ጥሪውና ያስተላልፋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ካልሆነ ግን የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅና ህገመንግስታዊ ስርዐቱን ለማስጠበቅ ሲል መንግስት ትጥቅ የማስፈታቱን ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡

መንግስት ህግን የማስከበር ስራውን በቆራጥነት ስለሚሰራ መላው ህዝብ የደህንነት ችግር ይገጥመኛል በማለት ስጋት ላይ እንዳይወድቅና እንዳይደናገር አቶ ካሳሁን መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ /የኢፌዴሪ መ/ኮ/ጉ/ጽ/ቤት/