በስራ ላይ የቆየውን የፀረ ሽብር አዋጅ ለማሻሻል ለወራት ሲደረግ የነበረው ጥናት ተጠናቆ ለውይይት ቀረበ

ባለፉት አስር አመታት በስራ ላይ የቆየውን የፀረ ሽብር አዋጅ ለማሻሻል በፌደራል አቃቤ ህግ የህግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ ለወራት ሲያደርግ የነበረውን ጥናት አጠናቆ ተጨማሪ ለማሰባሰብና በባለድርሻ አካላት ለማስተቸት የጥናቱን ውጤት ለውይይት አቅርበዋል፡፡

በጥናቱም በ2001 ዓ.ም የፀደቀው የኢትዮጵያ የፀረ ሽብር ህግ በርካታ ክፍተቶች ያሉበት መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በተለይም የዜጎችን ሰብዓዊም ሆነ ዴሚክራሲያዊ መብቶችን የጣሰና በርካቶችን ለእንግልት የዳረገ ነበረ ተብሏል፡፡

በዚህም ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ዋንኞቹ ሰለባዎች እንደነበሩ ተጠቅሰዋል፡፡

አተገባበርን በተመለከተ ህጎቹ በዘፈቀደ መተግበራቸውና የፍትህ አካላትም በአግባ ህጎቹን ከማስተግበር አንፃር ከፍተኛ ክፍተት ነበረባቸው ተብለዋል፡፡

የብሔራዊ ደህንነት መስሪያ ቤቱ ከህጋዊ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ በዜጎች ላይ አላስፈላጊ ምርመራዎችንና ግንኙነታቸውን ሲጠልፍ እንደነበርና አዋጁ ለተቋሙ የሰጠው ስልጣን የተጋነነ እና አተገባበሩም ክፍተት የነበረበት እንደነሆነ በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም ብሔራዊ ደህንነት መስሪያ ቤቱ በህግ ከተሰጠው ኃላፊነት አልፎ የፖሊስንና የሌሎች የፍትህ አካላትን ኃላፊነትም ያለአግባብ ሲጠቀም ነበር ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል የፌደራል ፖሊስ አቃቤ ህግ እና ፍርድ ቤቶችም የሽብር ተጠርጣሪዎች ላይ የነበራቸው አያያዝ የተዛባ ስለመሆኑ ተነስተዋል፡፡

ፖሊስ በማረሚያ ቤቶች እስረኞች ላይ አላስፈላጊ ድብደባዎችንና እንግልቶችን ሲያደርስ ና ፍርድ ቤቶች ደግሞ የሽብር ክሶች ጊዚያቸው እንዲራዘም በማድረግና ፍትሃዊነት የጎደለውን ፍርድ ሲሰጡ መቆየታቸው በጥናቱ ተዳሰዋል፡፡

ዋልታ ያነጋገራቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች ጥናቱ ከሞላ ጎደል ችግሮች በጥልቀት የዳሰሰ መሆኑን ገልጸው ለቀጣይ የዲሞክራሲ ግንባታ ህዴትም አስተዋፅኦ የጎላ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ሆኖም በቀጣይ አህጉራዊም ሆኑ አለምዓቀፋዊ ህጎችንና ልምዶችን በመቀመር መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች በቀጣይ ሊካተቱ ይገባዋል ብለዋል፡፡

ጥናቱን ያካሄደው የህግና የፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ በቀጣይ ሊወሰዱ ይችላሉ ያላቸውን ሁለት አማራጮች ያቀረቡ ሲሆን እነሱም የፀረ ሽብር ህጉን ሙሉ በሙሉ መሰረዝ አሊያም አዋጁ ያላቸውን ችግሮች ቀርፎ አሻሽሎ ማቅረብ የሚሉ ሃሳቦች ሲሆኑ የውይይቱ ተሳታፊዎች ሃሳብና አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡