ህገ ወጥ ወታደራዊ ሥልጠና ሲወስዱ የነበሩ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት አስታወቀ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህገ ወጥ ወታደራዊ ስልጠና ሲወስዱ በነበሩ ፀረ ሰላም ኃይሎች ላይ እርምጃ መዉሰዱን የክልሉ መንግስት አስታወቀ፡፡ 

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰይፈዲን ሃሩን እንደተናገሩት በህዝቡ ጥቆማ  በአሶሳ ወረዳ ገንገን ቀበሌ ልዩ ቦታዉ ዛለን ወንዝ በሚባል ስፍራ በተደራጀ መልኩ ወታደራዊ ስልጠና ሲወስዱ የነበሩ የጥፋት ኃይሎች ላይ የክልሉ ልዩ ሃይል ፖሊስ እርምጃ ወስዷል፡፡

በተደረገዉ ወታደራዊ ኦፕሬሽን 31 የሚሆኑ የጥፋት ሃይሎችን በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ የሰልጣኝ ቤቶች እንዲወድሙ ተደርጓል ብለዋል፡፡ 
ከ20 በላይ የሚሆኑ ወጣቶች ደግሞ በፈቃደኝነት እጃቸዉን መስጠታቸዉንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

ስልጠናዉን የሚወስዱት በተደራጀ ካምፕ ውስጥ የነበረ ሲሆን የህክምናና የምግብ አገልግሎት በተሟላ መልኩ ይቀርብ እንደነበር መታወቁን የገለፁት ኮሚሽነሩ ልዩ ኃይሉ በወሰደዉ እርምጃ ካምፑን ሙሉ በሙሉ መደምሰስ ተችሏል ብለዋል፡፡

የጥፋት ሃይሎች ዓላማ የክልሉን ሰላም ማደፍረስና የተለያዩ የጥፋት አጀንዳዎችን በማንገብ ህብረተሰቡ የተረጋጋ ኑሮ እንዳይኖር ማድረግ መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

ለኮሚሽኑ በደረሰዉ መረጃ መሰረት ከ4 መቶ በላይ የሚሆኑ የጥፋት ሃይሎች በተደራጀ መልኩ ከ 1 ወር በላይ ህገ ወጥ ወታደራዊ ስልጠና ሲወስዱ እንደነበር ታዉቋል ብለዋል፡፡

ሸሽተዉ ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን ብሉ ናይል ግዛት የገቡትን በቁጥጥር ስር ለማዋል የኦፕሬሽን ስራዉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

አብዛኞቹ የጥፋት ኃይል ሰልጣኞች 10 ዓመት ከዚያ በላይ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ታዳጊና ጎልማሶች ናቸዉ፡፡ በጥፋት ሃይሎች ወታደራዊ ስልጠና ዉስጥ ከመመልመል አንስቶ እስከ የጦር ትጥቅና የፋይናንስ ድጋፍ ያደረጉ አካላት የመለየት ስራ እየተሰራ ነዉ ብለዋል፡፡