ሰንደቅ ዓላማችን በህዝቦች መስዋትነት ያስጠበቅነው የነጻነታችን ምልክት ነው -ፕሬዚደንት ሙላቱ ተሾመ

የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ህዝቦች በከፈሉት መስዋትነት ያስጠበቅነው  የነጻነታችን  ምልክት  ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ  ተናገሩ ።

ፕሬዚደንት ሙላቱ ተሾመ በዛሬው ዕለት በህዝበ ተወካዮች  ምክር ቤት በተከበረው  የ11ኛው  የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር  ሰንደቅ ዓላማው በመፈቃቀድ ላይ የመሠረትነው የዴሞክራሲያዊ አንድነታችን ቃልኪዳን ማህተብ ነው ብለዋል ።

ለሰንደቅ ዓላማው ክብር  አኩሪ መስዋትነት እየከፈሉ ነጻ አገር ላስረከቡን ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችንን  አደራ  እያስታወስን የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓልን ማክበር ይኖርብናል ብለዋል ፕሬዚደንቱ በንግግራቸው።

ፕሬዚደንት ሙላቱ እንዳሉት ሰንደቅ ዓላማው የብሔር ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለዘላቂ ሰላም ፣ ለእኩልነትና ለዴሞክራሲያዊ አንድነት  ምልክት  እንዲሆናቸው ዳግም ቃልኪዳን  የገቡበት  አርማ መሆኑም አያይዘው ገልጸዋል ።

ባለፉት ዓመታትም መንግሥት  የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብና ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን  ታሪክ ለመቀየር  ከፍተኛ  የኢኮኖሚ ለውጥ ለማምጣትም  ጥረት ሲደረግ  መቆየቱን   ፕሬዚዳንቱ  ተናግረዋል ።

የአገሪቱ ክብርን  ለመመለስና ሁለንተናዊ  አገራዊ  ለውጥን ለማረጋገጥም  የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን  ዕቅድ ተግባራዊ በማድረግ  ፈጣን  የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማምጣት  እንቅስቃሴ  ሲደረግ  ቆይቷል ብለዋል ።

ባለፉት 27 ዓመታት ኢኮኖሚ ለውጥ  ለማምጣት  ጥረት  እንደተደረገ ሁሉ  የፖለቲካዊ ምህዳሩን ለማስፋትና የዜጎች  ህዝባዊ ተጠቃሚነትን  ለማረጋገጥ  በቂ ሥራዎች  ባለመካሄዳቸው ህዘቡ የተለያዩ ጥያቄዎችን እንዲያነሳ ምክንያት መሆኑን ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል ።

 መንግሥት  በአገሪቱ  የተፈጠሩ ችግሮችን በመለየትም የዜጎች  የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን  ለማስተናገድ  ከፍተኛ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑንም ፕሬዚደንቱ ጠቁመዋል ።

የዘንድሮው የሰንደቅ ዓለማ ቀን “ሰንደቅ አላማችን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችን” በሚል መሪ ቃል ለ11ኛ ጊዜ በተለያዩ  የአገሪቱ ህዝባዊ  ተቋማት በመከበር ላይ ይገኛል  ።

በመጨረሻም  የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በየዓመቱ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት እንዲከበር ለሚያደርጉት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ሌሎች አጋር አካላትን ፕሬዚዳንቱ ምስጋና አቅርበዋል ።

በዓሉን  የተጀመረው አገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ እንዲሳካ ትልቅ ጉልበት እንደሚሆን እምነታቸው መሆኑን በሥነሥርዓቱ ላይ ገልጸዋል ።