በዜጎች ላይ የተፈጠረው የመፈናቀልና የግድያ ተግባር የፖለቲካ አላማ ያላቸው አካላት የፈጸሙት ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

በአገሪቱ በዜጎች ላይ የተፈጠረው የመፈናቀልና  የግድያ ተግባር  የፖለቲካ አላማ ያላቸው የተደራጁ  አካላት የፈጸሙት  ሴራ  መሆኑን  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት  ተናግረዋል ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ በዛሬው ዕለት ፕሬዚደንት  ሙላቱ  ተሾመ ለህዝብ ተወካዮች እና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ የመክፈቻ ወቅት ያቀረቡትን  የ2011 ሞሽን  በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎችና አስተያየት ምላሽ ሠጥተዋል ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ሲያጋጥሙ የነበሩት  የዜጎች መፈናቀል እና ግድያ አስነዋሪና ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የተፈተነችበት ጊዜ መሆኑንም ገልጸዋል ፡፡

በኢትዮጵያ ዜጎች የታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዜጎች በራሳቸው  ዜጎች የተፈፀመው ግድያና መፈናቀል የሀገሪቱ የወደፊት ጥቁር ጠባሳ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዜጎች ላይ የተፈፀመው ጥቃትና መፈናቀል እንዲሁም ግድያ  በአፋጣኝ  ሊቆም የሚገባው ተግባር ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ይህ ችግሩ እንዳይስፋፋ ሰፊ ጥረት ማድረጉን የገለጹት ዶክተር አብይ አህመድ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተፈፀሙት መፈናቀሎችና ግድያዎች  በባለሙያዎች  ሳይጠና “የዘር ማጥፋት ጥቃት” ብሎ መፈረጅ አስቸጋሪ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እየታዬ ያለው ስርዓት አልበኝነት መንግስትና ህዝብ እየተፈተነበት ያለ ትልቅ ችግር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ነገር በጥንቃቄ መሻገር ካልተቻለ እንደሀገር ለመቆየት አሳሳቢ ነው ብለዋል፡፡

ካለፉት ስድስት ወራት ጀምሮ መንግስት በሀገሪቱ ሰላም ለማስፈን በሶስት መንገዶች የግጭትና መፈናቀል ችግሩን ለመፍታት እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን  ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጠቁመዋል ።

መንግሥት  ግጭትን ለማስቆም የግጭት አፈታት ዜደን፣ እምቅ የግጭት አቅም ያላቸውን ቦታዎች  ለይቶ በመከላከል የግጭት መነሻዎችን ማምከን እና ዘላቂ ሰላም የማስፈን ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከወንጀል ጋር ተያይዘው የሚጠረጠሩ ግለሰቦች ለህግ አለመቅረባቸውን በሚመለከት ለህግ ለማቅረብ ዝርዝር መረጃ እንደሚያስፈልግ እና የተጣራ ሙሉ መረጃ ያላባቸውን ግለሰቦችን  ለህግ የማቅረብ ስራ እየተሰራ እንደሆነና በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

ምክር ቤቱ የፕሬዚዳንቱን የመክፈቻ ንግግር ወይም ሞሽን አስመልክቶ የቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በጠቅላይ ሚንስትሩ ምላሽ ከተሠጣቸውና የመንግስትን አቋም ከተገለጸ በኋላ  የድጋፍ ሞሽኑን በሙሉ ድምፅ አጽድቀዋል፡፡