ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ ከጥቅምት 21 ጀምሮ በፈረንሳይና ጀርመን ጉብኝት ያደርጋሉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከጥቅምት 21 ጀምሮ በፈረንሳይና ጀርመን ጉብኝት ሊያደረጉ መሆኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ  ፡፡    

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም በሠጡት መግለጫ እንደተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአውሮፓ በሚኖራቸው ቆይታ ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኤማኑኤል ማክሮን እና ከጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ጋር በተለያዩ የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደርጋሉ ፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ በጀርመን ፍራንክፈርት በሚኖራቸው ቆይታም 25ሺህ ከሚሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ጋርም እንደሚወያዩ ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል  ፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ በጀርመን ነዋሪ ከሆኑት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ጋር የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ እንዲሁም በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መጥተው ባላቸው እውቀትና ገንዝብ ስለሚሠሩበት ሁኔታም ውይይት እንደሚደረግ ተገልጿል ።

እንደ ቃልአቀባዩ ገለጻ  የዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶችና ተቋማት በአፍሪካ  ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት  ያላቸውም ፍላጎት በመጨመሩ ጠቅላይ ሚንስትሩ በአውሮፓ ቆይታቸው  ከአይኤም ኤፍ ኃላፊዎችም ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ብለዋል ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ በፈረንሳይና ጀርመን ለሚያደርጉትም የሥራ ጉብኝትም ኢምባሲዎችና የዲያስፖራ  ማህበራት  ሙሉ  ዝግጅት ማጠናቀቃቸውም ተገልጿል ።