ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ከሁሉም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በሚጠበቁ ዕቅዶች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጡ

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሁሉም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች መካተት በሚገባቸው  ዕቅዶች  ዙሪያ ማብራሪያ  ሠጥተዋል ።

በጠቅላይ ሚንስትር  ዶክተር አብይ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የከፍተኛ አመራሮች ስልጠና እና ውይይት በትላንትናው ዕለት መጠናቀቅን አስመልክተውም  ማብራሪያ ሠጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በማጠቃለያው ላይ እንደገለጹትም ከሁሉም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የሚጠበቁ ያሏቸውን ዋና ዋና የውጤት አመልካቾችን በመግለጽ እነዚህ በዝርዝር በየሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የ100 ቀናት ዕቅድ ውስጥ እንዲካተቱ በማለት አመራር ሠጥተዋል፡፡    

የተዋሃዱ የሚንስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ተጠሪዎችም ሆነ ሌላ የተልዕኮ ወይም የአደረጃጀት ለውጥ የተደረገባቸው ተቋማት ፈጥነው በማስተካከልና ለሰራተኞቻቸው በቂ ኦረንቴሽን በመስጠት ወደ ተግባር እንዲገቡ አሳስበዋል ። 

በቢሮና ንብረት ርክክብ ብዙ ጊዜ መባከን እንደሌለበትም አስገንዝበዋል::

በዚሁም፡-

1) የሰላም ሚኒስቴር :-

* ሰላምና ደህንነትን የማረጋገጥ

* ብሔራዊ መግባባትን የማስፈን

* ግጭቶችን የመፍታትና የማስወገድ

* የዲሞክራቲክ ተቋትማን አሰራር የማዘመን

2) የመከላከያ ሚኒስቴር:-

* ጠላት የመከላከል ብቃትን የማሳደግ

* ብቃት ያለው የመከላከያ የሰው ኃይል የማዘጋጀት

* ባህር ኃይልን የማደራጀት

3) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር:-

* ከጎረቤት እንዲሁም ከሌሎች ስትራቴጂክ ከሆኑ አገሮች ጋር ወዳጅነትን የማጠናከር 

*የዳያስፖራ ተሳትፎን በሙያም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የማጠናከር
* ውጭ የሚኖሩ ዜጎችን መብት የማስከበር

* የአገሪቱን ገጽታ የመገንባት 

* የዲፕሎማቶች እና የሌሎች ሙያተኞችን ስምሪትን የማሻሻል

4) የገንዘብ ሚኒስቴር

* የኃብት ምንጭን የማሳደግ

* ብድር የመክፈል አቅምን የማሻሻል: የኮሜርሺያል ብድር ወደ ኮንሴሽናል ብድር እንዲቀየር የመስራት

* ወደግል መዞር የሚገባቸውን ተቋትማት ህጉን ተከትሎ እንዲዛወሩ የማድረግ
* የዋጋ ንረትን /ግሽበትን የመቆጣጠር

5) ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ

* የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ

* የህግና ፍትህ ሪፎርምን በብቃት የመምራት (የሚሻሻሉ ህጎችን ማሻሻልን ጨምሮ) 
* የታራሚዎችን ሰብዓዊ መብት የማክበር: በህጉ መሰረትም እንዲታረሙ የማድረግ

6) ግብርና ሚኒስቴር

* ዘርፉ በርካታ ተግባራትን በመያዝ የተደራጀ በመሆኑ በአግባቡ በሚ/ር መ/ቤቱ ውስጥም ሆነ ከሌሎች ጋር አቀናጅቶ የመምራት

* የግብርና ዘርፉን ምርታማነት የማሻሻል:

* የማዳበሪያ: የምርጥ ዘርና ሌሎችም ግብዓቶችን በወቅቱና በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ:

የሚሉት በምሳሌ ደረጃ ተጠቃሽ ናቸው::

በመጨረሻም በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች እና ሠራተኞች የስራ ጊዜን በማይሻማ መልኩ ከየተልዕኮአቸው ጋር የተቃኘ ስልጠና ሊሰጥ እንደሚገባ ተገልጾ የሁለት ቀን  ሥልጠናው እንደተጠናቀቀ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ በትዊተር ገጻቸው አስታውቋል፡፡