ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች በህገ-መንግሥቱ መሠረት እንዲፈቱ ሰማያዊ ፓርቲ ጥሪ አቀረበ

የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች በህገ-መንግሥት በተቀመጡ አቅጣጫዎችና መርሆች  መሠረት እንዲፈቱ  የሰማያዊ ፓርቲ ጥሪ አቀረበ  ።

የሰማያዊ  ፓርቲ  በዛሬው ዕለት በሠጠው መግለጫ እንደገለጸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችና በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ  የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎችን በህገ መንግሥቱ በተቀመጡ አቅጣጫዎች መሠረት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል ።

የአዲስ አበባ ህዝብ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ትግል ምዕራፍ ውስጥ ጉልህ  ሚና  ያለው መሆኑን የጠቆመው መግለጫው ለረጅም ጊዜ  መስዋትነት የከፈለው የአዲስ አበባ ህዝብ ጥያቄው በአግባቡ ተመልሶ የከፈለለትን መስዋትነትን የሚመጥን ቦታ  ማግኘት አልቻለም ብሏል ።

የአዲስ አበባ ነዋሪ መብቴ ተገፍቷል ማለቱን ተከትሎም በፖሊስ የተወሰደው  እርምጃና ከሕግ አግባብ  ውጪ በማሰር ለማሸማቀቅ የተደረገው ሁኔታ ፍጹም ሥርዓት የጣሰና ያለፈውን መንገድ ቆም ብለን እንድናሰብ የሚያደርግ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።

በአገሪቱ  የተለያዩ  አካባቢዎች ዜጎች የአስተዳደርና የማንነት ጥያቄ በማንሳት ላይ ናቸው ያለው  መግለጫው የማንነት ጥያቄዎችን በጠመንጃ ኃይል ምላሽ ለመሥጠት የሚደረገውን የትኛውንም አካሄድን  ሰማያዊ  ፓርቲ  አጥብቆ ያወግዛል ብሏል ።

በተጨማሪም በሐረር ከተማ ግለሰቦች በፈጠሩት ችግር  ዜጎች  ለውሃ  ጥም ተዳርገዋል  በቆሻሻ ክምርም መዋጧን ያመለከተው መግለጫው  የመንግሥት አካል ሳይውል ያሳድር ለጉዳዩ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሠጥ ሰማያዊ ፓርቲ ጥሪ አድርጓል ።

ሰማያዊ ፓርቲ በአገሪቱ ውስጥ  እየተደረገ ያለውን  ለውጥ የሚደግፈው በየትኛውም መልኩ ዜጎችን በእኩልነት የሚያይ ሥርዓት እስከሰፈነ ብቻ  መሆኑንም  በመግለጫው  አመልክቷል ።