የራያ ህዝብ የማንነት ጥያቄ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አልመጣም-የፌዴሬሽን ምክር ቤት

የራያ ህዝብ ማንነት ጥያቄ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ያመጣ አካል እንደሌለ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ትላንት ለ13ኛ ጊዜ ለሚከበረው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ በሠጡበት ወቅት እንደገለጹት በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች በህዝቦች መካከል ጥርጣሬና መቃቃር እየተፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።

የማንነት ጥያቄዎች ህዝብን ከህዝብ እያጋጨ መሆኑን ገልጸው፤ ምክር ቤቱ በማንነት ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ የማይሰጠው በክልል የሚደረጉ ተግባራት አሰራሮችን የማይከተሉ ስለሆነ መሆኑን አመላክተዋል።

ከሰሞኑ በአማራና ትግራይ ክልል አዋሳኝ ራያ አካባቢ በተከሰተው ግጭቶችና መፈናቀል ዙሪያ ለተጠየቁት ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ”የራያ ህዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አልመጣም” ብለዋል።

“የማንነቴ ይታወቅልኝ” ጥያቄ የሚስተናገድበት የራሱ ህገ መንግስታዊ አሠራርና ሂደት እንዳለው ጠቅሰው የማንነት ጥያቄ ሲቀርብ ስርዓትና ህገ መንግሰቱን መሰረት አድርጎ መጠየቅ፣ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድም መመለስ እንዳለበት ገልጸዋል።

የማንነት ጥያቄ  የሚያነሳ አካል መጀመሪያ ለወረዳ፣ ለክልል፣ ከዛም ክልል ካልመሰለው ደግሞ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በይግባኝ መልኩ ማቅረብ እንዳለበትም ተናግረዋል።

አሁን ላይ ያለው አካሄድ ግን ህገ መንግስቱን የተከተለ እንዳልሆነም አስረድተዋል።

”በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ያሉ የማንነት ጥያቄዎች የሚቀርቡት፣ ጠያቂውም የሚንገላታውና የሚሰቃየው በራሱ ክልል ነው” ያሉት አፈ ጉባኤዋ፤ የወልቃይትና የራያ ማንነት ጥያቄ ግን ከዚህ የተለየ እንደሆነ ገልጸዋል።

“ክልሉ የማንነት ጥያቄ ‘አይመለከትህም፣ መስፈርቱን አላሟላህም ካለ ጥያቄው ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤቱ በይግባኝ መጥቶ ምላሽ ይሰጥበታልም” ብለዋል።

ወልቃይቶች ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የአማራ ማንነት ጥያቄ ይዘው መምጣታቸውን አስታውሰው ምክር ቤቱም በክልል ማለፍ ያለባችውን ሥርዓት ተከትለው እንዲመጡ ምላሽ እንደሰጣቸውም ተናግረዋል።

የራያ ህዝብን በተመለከተ ግን “ጉዳዩን በግል ባውቀውም ህግና ስርዓቱን ተከትሎ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የመጣ ‘የማንነቴ ይታወቅልኝ’ ጥያቄ የለም” ብለዋል።

ሕዝቡ ጥያቄ ካለው ህግና ሥርዓቱ በሚጠይቀው አካሄድ ለትግራይ ክልል ማመልከትና ምላሽ ማግኘት እንደሚጠበቅበት ገልጸው ፌዴሬሽኑ ህግና ስርዓት ላልተከተለ ጥያቄ ምላሽ የመስጠት ኃላፊነት እንደሌለበትም አብራርተዋል። (ኢዜአ)