ፍርድ ቤቱ በነአብዲ መሀመድ ኡመር የክስ መዝገብ ላይ ለፖሊስ የ10 ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

ከነሀሴ 26 እስከ 30 2010 ዓ.ም በሶማሌ ክልል የተከሰተው ግድያ እና ዝርፊያ የቀድሞው የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ መሀመድ ኡመርን ጨምሮ ሌሎቹ የቀድሞ የክልሉ ባለስልጣናት ምርመራ እያካሄደ የሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ለተጨማሪ ምርመራ ከጠየቀው 14 ቀናት አስሩን የከፍተኛው ፍርድ ቤት ፈቅዷል፡፡

ፖሊስ ቀደም ሲል በተሰጠው የምርመራ ጊዜ ያከናወናቸውን ተግባራት ለፍርድ ቤቱ ያስረዳ ሲሆን ከተለያዩ ምንጮች የሚያገኛቸው መረጃዎች የበረከቱ ቢሆንም ግብረ አበሮችን ተከታትሎ ለመያዝ የክልሉ ስፋት የጎረቤት ሶማሊያ ድንበር መሆኑ እና በረሃማነቱ እንዳዳገተው አስረድቷል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ፖሊስ በተደጋጋሚ ጊዜ ለተመሳሳይ ምርመራ በየጊዜው ተጨማሪ ጊዜ መጠየቁ አግባብ አይደለም ሲሉ ተቃውሞ አሰምተዋል።

ጉዳዩን የተከታተለው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ የወንጀል ችሎት ጉዳዩን ካዳመጠ በኋላ 10 የምርመራ ቀን በመፍቀድ ለጥቅምት 29 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።