ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ተወያዩ

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ተወያዩ።

በፈረንሳይ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ትናንት ምሽት ነው በፓሪስ ኤልሴ ቤተ መንግስት ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር የተወያዩት።

በውይይታቸውም አጠቃላይ የሁለቱን አገሮች ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በመወያየት፤ በሀገራቱ መካከል ያለውን አጠቃላይ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከውይይቱ በኋላ በሠጡት መግለጫም፥ ሀገራቱ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ይህንኑ ሁለገብ ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ፅኑ ፍላጎት እንዳላት አስረድተዋል።

በውይይታቸው የላሊበላን አብያተ ክርስቲያናት የጥገና ሥራ ፈረንሳይ እንድትደግፍ፣ የፈረንሳይ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ከስምምነት መድረሳቸውንም አስረድተዋል።

እንዲሁም ለልማት የሚያግዝ ቀጥታ የበጀት ድጋፍ ለማድረግ፣ በፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ፣ በበዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) እና በአለም ባንክ በኩል በቀጥና በቦርድ በኩል ድጋፍ ለማድርግ መስማማታቸውንም ገልፀዋል። 

በአፍሪካ ቀንድ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የመጣውን ሰላም በማስቀጠል በኤርትራና በጅቡቲ መካከል ሰላም እንዲጠናከር ለማድረግ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውንም አስታውቀዋል።

ፕሬዚዳንት ማክሮን ኢትዮጵያን እንዲጎብኙ ግብዣ በቀረበላቸው መሰረት በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ጉብኝት እንደንደሚያደርጉ እና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩም አስታውቀዋል።

ፕሬዝዳንት ማክሮን በበኩላቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አስተዳደር በኢትዮጵያ የተጀመሩ ሁለገብ የማሻሻያ እርምጃዎችን እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ልማት እያበረከተች ያለውን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደንቁ ገልፀዋል።

በፈረንሳይ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በቀጣይም ወደ ጀርመን የሚያቀኑ መሆኑም ታውቋል።

በጀርመን ቆይታቸውም ከሀገሪቱ መራሄተ መንግስት አንጌላ ሜርክልና ከሌሎች የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር የሀገራቱን ሁለንተናዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጀርመን ከተመረጡ ግዙፍ የጀርመን ኩባንያዎች ጋርም እንደሚወያዩ ነው የተገለጸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በጀርመን ቆይታቸውም ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ.ም ከተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ከሚውጣጡ 25 ሺህ ኢትዮጵያውያን ጋር በፍራንክፈርት ይወያያሉ። 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአውሮፓ ጉብኝት “አንድ ሆነን እንነሳ ነገን በጋራ እንገንባ” በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ መሆኑም ተነግሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝቱን የሚያደርጉት በሀገራቱ መሪዎች በቀረበላቸው ግብዣ መሰረት ነው።(ኤፍ.ቢ.ሲ)