በኦነግ ስም በህብረተሰቡ ላይ ስጋት የደቀኑ ታጣቂዎች እጃቸውን ሊሰበስቡ ይገባል- አቶ ለማ መገርሳ

በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ስም በምዕራብና ቄለም ወለጋ አካባቢዎች  በህብረተሰቡ ላይ ስጋት የደቀኑ ታጣቂዎች በአስቸኳይ እጃቸውን ሊሰበስቡ እንደሚገባ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ አስጠነቀቁ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ  በወቅታዊ ክልላዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት  መንግሥት ጉዳዩን እስከ አሁን  በከፍተኛ ትዕግስት ሲመለከተው ቆይቷል፡፡

ከአሁን በኋላ ግን የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ህግ የማስከበር ስራ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

የሀገር ሽማግሌዎችና ህብረተሰቡ በድርጊቱ የሚሳተፉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ወደ ሰላማዊው መንገድ እንዲመለሱ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ርእሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የቤንሻንጉል ጉሙዝና የኦሮሚያ ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ችግር በአፋጣኝ ለመፍታት ተስማምተዋል፡፡

የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮችና ከፍተኛ ባለስልጣናት በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው ከስምምነት ላይ የደረሱት፡፡(ምንጭ:ኦቢኤን)