ብሄራዊ ዕርቅን በተመለከተ በመላው ኢትዮጵያ ዝርዝር ውይይት ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው–ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

​​​​​​ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ብሄራዊ ዕርቅን በተመለከተ በመላው ኢትዮጵያ ህግን የማወቅ፣ መብትና ግዴታን የመለየት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች የተካተቱበት ዝርዝር ውይይት ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጀርመን ፍራንክፈርት ኮሜርዝ ባንክ አሬና ስታዲየም ከተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች የመጡ ኢትዮጵያውያን ላቀረቡት ጥያቄ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡

በሀገሪቱ ካለው የሰላም ሁኔታ ጋር በተያያዘ፣ ስለህግ የበላይነት፣ ስለምርጫ ቦርድ፣ ስለዜጎች መፈናቀል፣ በፌደራልና በክልሎች ስላለው ጉዳይና ሌሎች በርካታ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸውም ጃፓን በአንድ ወቅት በአውሎ ንፋስ በተመታችበት ወቅት መልሰን ለመገንባት ዕድል አገኘን ማለታቸውን አስታውሰው፥ እኛም ሀገራችንን ለመገንባት አሁን ያሉትን ችግሮች እንደዕድል የምናስብ ከሆነ ተሻግረን እናልፋቸዋለን ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሰባት ወር በፊት እንደሀገር ከፍተኛ መናጥ ውስጥ ወድቃ እንደነበር አስታውሰው፥ ዛሬን ከዚያ ጊዜ ጋር አታመሳስሉት እንዲሁም የነገው ደግሞ እጅግ የተሻለ ነው ብለዋል፡፡

የህግ የበላይነትን በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄ የዘረፉ ሌቦች በህግ ፊት ማቅረብ ለኛ ግዴታ ብቻ ሳይሆን መሰል ተግባር እንዳይፈጸም ማስተማሪያም ጭምር ነው ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡

አንድነትን በተመለከተ የኢትዮጵያን አንድነት የሚገዳደሩ ኃይሎች በዘመናት መካከል የነበሩ ቢሆንም አንዳቸውም ማደናቀፍ ያለመቻላቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ብዙ ፍላጎቶች ቢኖሩም ነገርግን ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ሆና ትቀጥላለች ብለዋል፡፡

ስለመደመር በተነሳላቸው ጥያቄ በቅርቡ በመጽሐፍ መልኩ በዝርዝር እንደሚያቀርቡ ይፋ አድርገዋል፡፡

የፌደራልና የክልል መንግስታትን በተመለከተ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ፌደራሊዝም የመተዳደሪያ እንጂ የመለያያ መንገድ አይደለም የተከሰቱ ችግሮችም የለውጥ ጊዜ መንገራገጭ አድርገን ብንወስዳቸው ይሻላል ብለዋል፡፡

ክልል ብቻ ክፍለሀገር ብቻ ይሁን የሚሉ አስተሳሰቦች በመካረር ሳይሆን በመመካከር ነው ችግሩን መፍታት የሚቻለው ያሉ ሲሆን ዛሬ መመለስ የሚቻለውን ምላሽ እየሰጠን ለነገ የሚሆነውን ሰክነን እየመለስን እንሄዳለን ብለዋል፡፡

ከትጥቅ መፍታት ያለመፍታት ጋር በተያያዘ አንድም ተቃዋሚ ፓርቲ መሳሪያ ይዞ ወደ ሀገር ቤት አልገባም ብለዋል፡፡

ነገርግን አሁን ያለው መሳሪያ በተለያየ መልኩ በህገወጥ መልኩ የገቡ መሆናቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ ከኦነግ አመራሮች ጋርም ችግሩን ለመፍታት መወያየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ምርጫ ቦርድን በተመለከተም ማናችሁም በማትገምቱት መልኩ እየተደራጀ ነው ብለዋል፡፡

ከተለያዩ ሀገራት ጋር ተደርገዋል ስለተባሉ ስምምነቶች የተነሱላቸው ሲሆን ከኢትዮጵያ ህዝብ የሚደብቁት አንዳችም ነገር ያለመኖሩን አንስተው ከግብጽ፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ከሳዑዲ አረቢያ ጋር አዲስ የተፈራረሙት ስምምነት ያለመኖሩን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከ60ዎቹ ጀምሮ ጦርነቱን የሚቆሰቁሱት ኃይሎች ሳይሆኑ የሚሞቱት ተራው የገበሬ ልጅ እንደሆነ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከዚህ ቀደም ከነበረው ከ334 በመቶ በላይ መጨመሩን ገልጸዋል፡፡

የዓለም ባንክም ትናንት ይፋ ካደረገው የ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ እና ብድር በተጨማሪ ከሦስት ወራት በኋላም ሌላ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል መግባቱን አስታውቀዋል፡፡

ቋንቋን በተመለከተ ጣልያን በ1930ዎቹ ያስጠኑትን ጥናት በማስታወስ ሊወሩን ቢመጡም ዛሬ እኛ ከያዝነው የተሻለ ሐሳብ አቅርበው እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

በመጨረሻም ኦሮምኛ የፌደራል መንገስቱ ቋንቋ እንዲሆን አማራው መታገል አለበት አማርኛ ይበልጥ እንዲሻሻል አሮሞው መሞገት ይገባዋል ሲሉም ነው ያሳሰቡት፡፡ (ኤፍ.ቢ.ሲ)