አቶ ሽመልስ አብዲሳ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ተሾሙ

አቶ ሽመልስ አብዲሳ አቶ ፍጹም አረጋን በመተካት በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን ተሹመዋል፡፡

በተሰጣቸው የስራ ኃላፊነት መሰረት ፕሬስ ሴክሬተሪያት፣ ብሔራዊ የሰላም ጉዳይ አማካሪ፣ የስራብቃት እና ምዘና ፖሊሲ ፅ/ቤት እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤትን ይመራሉ፡፡

 አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከ2002 ጀምሮ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በተለያዩ ደረጃዎች ተመድበው ሰርተዋል፡፡ እስከ ዛሬ ድረስም የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ የኦሮሚያ ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ በነበሩበት ወቅት አቶ ሽመልስ የዶክተር አብይ ምክትል በመሆን አገልግለዋል።

አቶ ሽመልስ ከዘጠኙ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴዎች መካከል አንዱ በመሆን በድርጅታዊ ጉባኤው መመረጣቸው ይታወሳል።

በተጨማሪም አቶ ሽመልስ የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡

አቶ ሽመልሽ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰብአዊ መብት በማስተርስ ዲግሪ የተመረቁ ሲሆን ከደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ዩኒሳ ደግሞ  በፖለቲካ ፍልስፍና በማስተርስ ተመርቀዋል፡፡(ምንጭ: ኦቢኤን)