የምክር ቤቱ የቋሚ ኮሚቴዎች ቁጥር ከ20 ወደ 10 ዝቅ እንዲል ተደረገ

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ስብሰባውን በትናንትናው እለት አካሂዷል።

ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባውም የቋሚ ኮሚቴዎች አደረጃጀትን ለመወሰን የቀረበ የውሳኔ ሓሳብ ላይ ተወያይቶ አፀድቋል።

ለምክር ቤቱ ቀርቦ በፀደቀው በውሳኔ መሰረትን  ቀደም ሲል  20 የነበሩት የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ወደ 10 ዝቅ እንዲሉ መደረጉ ተገልጿል።

 አዲስ የተደራጁት 10  ቋሚ ኮሚቴዎች እያንዳንዳቸው በሥራቸው ከ2 እስከ 4 ንዑስ ኮሚቴዎች ማደራጀት እንደሚገባቸውም በውሳኔ ሀሳቡ ላይ ተገልጿል።

የቋሚ ኮሚቴዎች አደረጃጀት ማሻሻያ ማድረግ ያስፈለገበት  ዋና ምክንያት መንግስት ለሚሠራው ስራ የላቀ ውጤታማነት ለመረጋገጥ መሆኑ ተገልጿል።

የምክር ቤቱ ሕገ መንግስታዊ ተልዕኮ በተሟላ እንዲወጣ ለማስቻል ወሳኝ በመሆኑ እና የመንግስትን አደረጃጀት ክለሳ ተከትሎ የሚደራጅ ማሻሻያ እንደሆነም  በምክር ቤቱ ውይይት ወቅት ተጠቅሷል ።

ምክር ቤቱ አደረጃጀት ማሻሻያን መሠረት በማድረግ የቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት ምደባን በተመለከተ ሰፊ ውይይት በማድረግ የቀረበ የውሳኔ ሓሳብ መርምሮ በ2 ተቃውሞ በ6 ድምጽ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አጽድቆታል።

በምክር ቤቱ አንዲፀድቁ የተደረጉት10ሩ ቋሚ ኮሚቴዎች፦

  1. የህግ፣ ፍትህ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
  2. የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
  3. የሰው ሃብት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
  4. የሴቶች፣ወጣቶችና ማህበራ ዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
  5. የተፈጥሮ ሃብት፣መስኖ እና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
  6. የከተማ ልማት፣ኮንስትራክሽን እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
  7. የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
  8. የገቢዎች፣በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
  9. የግብርና፣ አርብቶ አደር እና አከባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
  10. የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ

እያንዳንዱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሚኖሩት ሲሆን አጠቃላይ የአባላት ብዛትም ከ20 እስከ 45 የሚደረስ ነው።