ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ ለኢኮኖሚ ትብብርና ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል

የኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ መሪዎች ትናንት በባህር ዳር በሶስትዮሽ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሃመድ አብዱላሂ በውይይታቸው የኢኮኖሚ ትብብርና የአፍሪካ ቀንድን ሰላምና ደህንነት በማጠናከር ረገድ ከስምምነት መድረሳቸውን ነው የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያስታወቀው።

ኢትዮጵያ፣ኤርትራና ሶማሊያ በጋራ ያቀዱት የኢኮኖሚ ውህደት በታቀደው መልክ እየተከናወነ መሆኑን መሪዎቹ አስታውቀዋል።

መሪዎቹ ከሰዓታት በፊት በጋራ በሰጡት መግለጫ፥ የኢኮኖሚ ትብብርና ቀጠናዊ ሰላምን የማስጠበቅ እቅድ በሚገባ እየተተገበረ መሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ፥ከሁለት ወር በፊት በጋራ በነደፉት እቅድ አተገባበር ላይ ውይይት መካሄዱን አንስተው እቅዱ በተቀመጠው ልክ እየተተገበረ ይገኛል የሚል ድምዳሜ ላይ መደረሱን አስታውቀዋል።

መሪዎቹ ቀጣዩ የሶስትዮሽ ውይይት በሶማሊያ ሞቃዲሾ እንዲካሄድም ውሳኔ አሳልፈዋል።
በዳዊት መስፍን

መሪዎቹ በአለም አቀፍ ጉዳዮች ላይም በተቀናጀና በተጠናከረ መልኩ አብሮ ለመስራትም ተስማምተዋል።

የመሪዎቹ ውይይት ዛሬም እንደሚቀጥል ተመልክቷል።

መሪዎቹ የአማራ ክልል ጉብኝትን ከጎንደር በመጀመር ትናንት ከሰዓት በኋላ ነበር ባህር ዳር የገቡት።

ማምሻውን በተከናወነ የእንኳን ደህና መጣችሁ ዝግጅትም ለመሪዎቹ የተለያዩ ስጦታዎች ተበርክተዋል።(ኤፍቢሲ)