የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ታራሚዎችን ጎበኙ

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ታራሚዎችን ጎብኝተዋል፡፡

በዛሬው ዕለት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት፣ የፌደራል አቃቢ ህግ፣የፌደራል ፖሊስ እና ሌሎች የፍርድ ቤቶች ከፍተኛ ኃላፊዎች የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ታራሚዎችን በመጎኘት ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ወቅትም ታራሚዎቹ በፍትህ ሥርዓቱ፣ በማረሚያ ቤት አገልግሎት አሰጣጥ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ችግሮች እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል።

ታራሚዎቹ ከፍትህ ሥርዓቱ ጋር ተያይዞ ወንጀለኛ ያልሆነን ግለሰብ ለፍርድ የማቅረብና አላግባብ የማሰር እንዲሁም ትክክለኛና አግባብ የሆነ ፍትህ ከመሥጠት አንጻር ችግሮች መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ይቅርታ ተደርጎላቸው በማይታወቅ ምክንያት በድጋሚ ወደ ማረሚያ ቤት የገቡ ታራሚዎች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።

ታራሚዎች ላይ የሚደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉዳይም ለሚዲያ ፍጆታ ከመዋል ባለፈ አለመስተካከሉን ጠቅሰው ችግሩ እልባት እንዲያገኝ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም በማረሚያ ቤቱ ውስጥ በአገልግሎት አሠጣጥ ላይ ችግሮች እንደሚስተዋሉም በውይይታቸው አንስተዋል፡፡

ታራሚዎቹ ከህክምና አገልግሎት አሰጣጥ፣ ከምግብ አገልግሎት እና ከወላጆቻቸው ጋር ማረሚያ ቤት ለገቡ ህጻናት የትምህርት እድልን ከማመቻቸት አንጻር ችግሮች እንደሚስተዋሉም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አንጻርም ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄ እንዲሰጣቸውም ነው የጠየቁት።

ከታራሚዎቹ ለተነሱት ጥያቂዎች ምላሽ የሰጡት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ለበርካታ አመታት ሲንከባለል የቆየውን የፍትህ ጥሰት ችግር ለመቅረፍ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ከታራሚዎች አያያዝ ጋር በተያያዘ ምላሽ የሠጡት የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ዋና አስተዳደር ኃላፊ አቶ ጀማል አባሱ ከአቅም ውስንነት ጋር ተያይዞ የማረሚያ ቤቶች ችግሮችን ለመቅረፍ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የሚነሱ ችግሮችን መንግስት እንዲገነዘበው በማድረግ በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡