በውጭ አገራት የሚኖሩ ዜጎችን መብት ለማስጠበቅ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል ተባለ

በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስትር ዴኤታዎቹ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ እና ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል በመካከለኛው ምስራቅ የኢትዮጵያ ሚሲዮን መሪዎችና ቆንስላ ጀኔራል ጽህፈት ቤቶች ኃላፊዎች እንዲሁም የዜጎችን ጉዳይ ከሚከታተሉ ዲፕሎማቶች ጋር ተወያይተዋል።

በሚኒስቴሩና ዓለም አቀፉ የስራ ድርጅት (ILO) ትብብር በሊባኖስ የተዘጋጀው ውይይቱ ያተኮረው፤ ሚሲዮኖች በተወከሉባቸው አገራት በኢትዮጵያውያን ዜጎች መብት አከባበርና እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች ዙሪያ ነው።

በዚሁ ወቅት ሚሲዮኖች በዜጎች መብት አጠባበቅ ዙሪያ ያከናወኗቸውን ተግባራት፣ የገጠሟቸውን ችግሮችና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎችን ሪፖርት አቅርበው ውይይት እንደተረገባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ባለስልጣናቱ ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ የስራ ስምሪት ስምምነት ከተፈረመባቸው ሳውዲ አረቢያ፣ ኳታርና ጆርዳን ጋር የስራ ስምሪቱን መጀመር በሚቻልበት መንገድ ላይ እየተደረገ ያለውን ጥረትም አብራርተዋል።

ስምምነት ካልተፈረመባቸው የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ፣ ኩዌት፣ ሊባኖስ፣ ባህሬንና ኦማን ጋር ደግሞ የተጀመሩ የድርድር ሂደቶች ያሉበት ደረጃ በውይይቱ ትኩረት ተሰጥቶ ተመክሮበታል።

ሚኒስትር ዴኤታዎቹ በመካከለኛው ምስራቅ አገራት በሚገኙ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን የመብት ጥሰት ለማስቀረት መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች እና በመጪዎቹ 100 ቀናት ዕቅድ ውስጥ ተካተው መመለስ ስላለባቸው ጉዳዮች ለሚሲዮን መሪዎች መመሪያ ሰጥተዋል።

በውጭ አገራት የሚገኙ ዜጎችን መብትና ደህንነት ማስጠበቅ በመንግስት ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ባለስልጣናቱ በዚሁ ወቅት አረጋግጠዋል።

በመካከለኛው ምስራቅ አገራት የሚገኙ ሚሲዮኖችም በዚሁ መሰረት ትኩረት ሰጥተው እንዲንቀሳቀሱ አሳስበዋል፡፡

በቀጣዮቹ ቀናትም በሁለትዮሽ የስራ ስምሪት ስምምነት ምንነትና የድርድር ሂደት ላይ ስልጠና ይሰጣል ተብሏል። (ኢዜአ)