የወጣቶችን ስራ አጥነት ለመቀነስ ከአውሮፓ ህብረት ጋር መግባባት መደረሱን ዶ/ር ወርቅነህ ገለፁ

በኢትዮጵያና በአውሮፓ ህብረት መካከል ያለው ግንኙነትና ሁለገብ ትብብር ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ገለፁ።

ሚኒስትሩ የአውሮፓ ህብረት የፍልሰትና ዜግነት ጉዳዮች ኮሚሽነር ዲሚትሪስ አቫምፖለስ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በዚህ ወቅት በሀገሪቱ  የተደረጉ አጠቃላይ ማሻሻያዎችን፣ ሀገራዊና ቀጠናዊ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮችን በሚመለከት ተወያይተዋል። 

በህብረቱና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ሁለገብ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግም መግባባት ላይ ደረሰዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአፍሪካ ዋና የፍልሰት ምንጭ  የወጣቶች ሥራ አጥነት  መሆኑን በመጥቀስ  በወጣቶች ሥራ ፈጠራ ላይ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያለውን ትብብር ለማስፋት መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

እንዲሁም ህገ-ወጥ ፍልሰት ለመከላከልና በህጋዊ መንገድ ወደ አውሮፓ የሚደረጉ የወጣቶች የስራ ስምሪትን ከማሳደግ አንጻር ከህብረቱ ጋር በጋራ ለመሥራት መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

ዶክተር ወርቅነህ ከኤርትራ ጋር የተጀመረው የሰላም ሂደት ለቀጠናዊ ሰላምና አጠቃላይ ትብብር ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

በሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ያለው ሁኔታም ከፍተኛ መሻሻል እያሳየ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፥ ሂደቱ አስተማማኝና ዘላቂ እንዲሆን ትብብራቸውን ለማስፋት ተስማምተናል።

ኮሚሽነር ዲሚትሪስ በበኩላቸው በየትኛውም አካባቢ አዲስ ለውጥና ማሻሻያ ሲደረግ ሂደቱ አድካሚ እንደሚሆን ገልጸው ህብረቱ በሀገሪቱ የተጀመረውን ሁለገብ ማሻሻያና ለውጥ እንደሚያደንቅና ለስኬታማነቱ የተጠናከረ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ህብረቱ ህገ-ወጥ ፍልሰትን ከመቆጣጠር ጎን ለጎን በህጋዊ የሥራ ስምሪት ከኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ የሚደረግን ህጋዊ ዝውውር እንዲሰፋ ይፈልጋልም ብለዋል።

ኢትዮጵያና ህብረቱ በቀጠናዊ ሰላምና ፀጥታም  ያላቸው  ትብብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።(ኤፍ. ቢ. ሲ.)