የቀድሞው የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ኃላፊ አቶ ያሬድ ዘሪሁን በቁጥጥር ሥር ዋሉ

የቀድሞው የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ኃላፊ እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል የነበሩት  አቶ ያሬድ ዘሪሁን በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለመገናኛ ብዙሃን እንደገለፀው ፥ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር የዋሉት በትናንትናው ዕለት ነው።

በተያያዘ  ዜና የቀድሞውን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራል አቶ ያሬድ ዘሪሁንን አስመልጠዋል በሚል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በትናንት ዕለት  ፍርድ ቤት  ቀርበዋል።

በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት አቶ ያሬድን አስመልጠዋል የተባሉት የነብስ አባቱ አባ ኃይለማርያም ኃይለሚካኤል እና ሾፌራቸው አሸናፊ ታደለ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪውን ለመያዝ ተጨማሪ የማጣራት ሥራዎችን ለማከናወን  ችሎቱን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል።

ችሎቱም መርማሪ ፖሊስ ያቀረበው ሓሳብ ተቀባይነት የለውም በሚል ፖሊስ በ10 ቀን ውስጥ አጣርቶ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ሰሞኑን በሙስናና በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ ከ60 የሚበልጡ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወቃል።