ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ጋር ተወያዩ

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከግብፁ አቻቸው ሳሚ ሽኩሪ ጋር ከአፍሪካ ህብረት የሚኒስትሮች አስቸኳይ ጉባዔ ጎን ለጎን በዛሬው ዕለት በተለያዩ ጉዳዮች  ላይ  ውይይት አድርገዋል፡፡                                

በውይይቱም ሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠል ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች የጎላ ጠቀሜታ እንዳለውም ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተናግረዋል፡፡

የግብጹ ውጭ ጉዳይ  ሚንስትር  በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በምስራቅ አፍሪካ የጀመሩት የሰላም ሂደት ለቀጠናው ሰላምና ብልፅግና ገንቢ ሚና ያለው መሆኑን አንስተዋል፡፡

ሚኒስትሮቹ በህዳሴ ግድብ ላይ እየተካሄዱ ባሉ ሁለት ጥናቶች ላይም ውይይት በማድረግ ፣ጥናቶቹ በሚጠናቀቁበት ሁኔታ ላይም የመፍትሄ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

የህዳሴ ግድብን አሞላል በተመለከተ የሶስቱ ሀገራት የሳይንቲስቶች ቡድን እስካሁን ያደረጉትን የስራ እንቅስቃሴ ያደነቁ ሲሆን፥ በቀጣይ ኢትዮጵያ፣ግብፅና ሱዳን ከስምምነት በሚደርሱበት የግድቡ የአሞላል ሂደት ላይም  አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

በተጨማሪም በሶስትዮሽ የመሰረተ ልማት ፈንድ ትብብሩ ዙሪያ ሀሳብ በመለዋወጥ የሶስቱ ሀገራት የሚመለከታቸው ኃላፊዎች በቀጣይ ተገናኝተው የሚወያዩ መሆኑም ተመልክቷል ።(ምንጭ: የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት)