ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የመጣውን ለውጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል የበኩላቸውን ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ ሦስት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጹ ።
የአፋር ህዝቦች ፓርቲ፣ የአዲስ ትውልድ ፓርቲና አንድነት ፓርቲ አመራሮች ለዋልታ እንደገለጹት መንግሥት የጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ አጠናክሮ ለማስቀጠል ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይገባቸዋል ብለዋል ።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያሏቸውን የልዩነት ሓሳቦች ወደጎን በመተው አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም የፓርቲ አመራሮቹ ጥሪ አስተላልፈዋል ።
የአፋር ሕዝቦች ፓርቲ አመራር የሆኑት አቶ ሙሳ አደም እንደገለጹት ለህዝብ አገልግሎት እየሠጡ ያሉት በለውጡ አስተሳሰብ የተቃኙ ለማድረግ አስፈላጊውን ትምህርትና ሥልጠና መሥጠት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል ።
የአንድነት ፓርቲ አመራር የሆኑት አቶ ትዕግስቱ አወሉ በበኩላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የደረሰባቸው ዜጎችን መንግስት እራሱን የቻለ ተቋም በመመሥረት በኢኮኖሚም ሆነ በስነ ስነ ልቦና ረገድ ድጋፍ ሊያደርግላቸው ገባል ብለዋል ።
ሌላው የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ( አትፓ) አመራር የሆኑት አቶ ሰለሞን ደነቀ እንደገለጹት የተፎካካሪ ፓርቲዎችና አባሎቻቸው ሙስና በማጋለጥ ረገድ መንግሥት የጀመረውን እንቅስቃሴ በተግባር እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል ።