ፍርድ ቤቱ ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው በራሳቸው ጠበቃ እንዲያቆሙ ወሰነ

ፍርድ ቤቱ ለሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው የመከላከያ ጠበቃ ለማቆም  ያስተላለፈውን  ውሳኔ በማንሳት በራሳቸው ጠበቃ እንዲያቆሙ ትናንት በዋለው ችሎት ላይ ወሰነ ።

ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ከትናንት በስተያ ተከላካይ ጠበቃ እንዲቆምላቸው ትዕዛዝ የሠጠው የከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ አስረኛ ምድብ ችሎት ፖሊስ ተጠርጣሪው ጠበቃ በግላቸው ማቆም እንደሚችሉ ባቀረበው ማስረጃ ምክንያት ትዕዛዙን  ውድቅ አደረጓል ፡፡

መርማሪ ፖሊስ የቀድሞ የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የቀድሞው ኃላፊ በስማቸው ቤት መኪና እና በሂሳብ ቁጥራቸው ያለ አምስት ሺ ሶስት መቶ ገደማ ብር መገኘቱን ለችሎቱ ማስረጃ አቅርቧል፡፡   

ሜጀር ጀነራል ክንፈ ቀደም ሲል በፌደራል ፀረ ሙስናና ስነ ምግባር ኮሚሽን ያስመዘገቡትን ሀብት፣ 80 ሺህ የሚያወጣ ተሸከርካሪ እና ቢሾፍቱ ከተማ ላይ መኖሪያ ቤት እንደዚሁም የተለያዩ የአክሲዮን ድርሻዎች እንዳላቸው መርማሪ ፖሊስ በማስረጃነት ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።

በተጨማሪም በአዋሽ ባንክ እስከ ህዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ያላቸውን ተቀማጭ ሂሳብ በማስረጃነት  ያቀረበ ሲሆን ከአስራ አምስት ቀን በፊት ተጠርጣሪው ከሂሳቡ አንድ መቶ ሺ ብር ስለማውጣቸውም የሚያሳይ ማስረጃ በፖሊስ ቀርቧል፡፡ 

 ፍርድ ቤቱ የባንክ ሂሳባቸው ሲታይ በፈረንጆቹ በ24/10/2018 100 ሺህ ብር አስገብተው በ29/10/2018 100 ሺህ ብር ወጪ ማድረጋቸውን ተመልክቷል።  

መርማሪ ፖሊስም ይህ ሀብታቸውን ለማሸሽ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ማሳያ ይሆናል ብሏል።

ግራና ቀኙን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ ገቢ እና ወጪ ያደረጉበት የቀን ልዩነት ያላቸው ሀብት ለመጥፋቱ ማሳያ ስለማይሆን ፍርድ ቤቱ የመከላከያ ጠበቃ ለማቆም  ያስተላላፈውን  የውሳኔ ሓሳብ እንስቷል ። 

በመጨረሻም ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው በበኩላቸው በግላቸው ጠበቃ ለመቅጠር ያቀረቡትን ጥያቄ ችሎቱ ተቀብሎ ጉዳዩን በቀጣይ ለመመልከት ለህዳር 10 ቀን 2011 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ተጠርጣሪው ፍርድ ቤቱን ቤተሰቦቼ መጥተው እንዲመለከቱኝ ይፍቀድልኝ የሚል ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፥ ፍርድ ቤቱም ጥያቄውን ለመፍቀድ መርማሪ ፖሊስ የቤተሰቦቻቸውን ህጋዊነት እና ተገቢነት አጣርቶ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ጋዜጠኛ ፍጹም የሺጥላ ባቀረበችው ጥያቄ መሰረት የመንግስት ተከላካይ ጠበቃ ቆሞላታል።