66ኛው የኢጋድ የሚኒስትሮች አስቸኳይ ምክር ቤት ስብሰባ ተጀመረ

66ኛው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) የሚኒስትሮች አስቸኳይ ምክር ቤት ስብሰባ በአዲስ አበባ ሸራተን አዲስ ተጀምሯል።

በአስቸኳይ ስብሰባው የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ በአዲስ አበባ የተፈራረሙትን የሰላም ስምምነት አፈጻጸምና እና በሶማሊያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እንሚመክር ተገልጿል።

የወቅቱ የኢጋድ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀመንበር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ባደረጉት ንግግር፥ ኢጋድ የአፍሪካ ቀንድን ወደ ህብረት ሊያደርሱ የሚያስችሉ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ በአካባቢ የአየር ሁኔታ፣ በደህንነት፣ በንግድ፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ መስኮች ያከናወናቸው ተግባራት ቀጠናውን ከፍ ወዳለ ማማ የሚያደርሱ ናቸው ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

ኢጋድ በደቡብ ሱዳን ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ ላይ ያለው ጥረት ውጤታማ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲመጣ አለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

በደቡብ ሱዳን የኢጋድ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ኢስማኤል ዋይስ የሃገሪቱን ሰላም ተግባራዊ ለማድረግ ቅድመ ሽግግር ኮሚቴው ጁባ ውስጥ ስራውን መጀመሩ በጎ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሶማሊያ የኢጋድ ልዩ ልዑክ ዶክተር ሞሃመድ ጉዮ በበኩላቸው የሶማሊያ ኢኮኖሚ እንዲያገግም በማድረግ እና ተቋማቱን በመገንባት ረገድ ብዙ ርቀት መሄዷን አንስተዋል።