አፍሪካ በዓለም ተወዳዳሪ ሆና እንድትገኝ አንድ ድምፅ ልታሰማ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ

የአፍሪካ ህብረት 11ኛው የመሪዎች አስቸኳይ ጉባኤ መክፈቻው ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ተወዳዳሪ ሆና ለመገኘት አንድ ድምፅ ልታሰማ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የመጀመሪያቸው በሆነው በህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ንግግራቸው ኢትዮጵያ በጥልቅ መታደስ ውስጥ እንዳለች በማንሳት ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ ለበርካታ ችግሮች ምላሽ የሚሆኑ የማሻሻያ እርምጃዎችን መውሰዷን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ምህዳር እየፈጠረች መሆኗን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን መፍታቷን፣ የመገናኛ በዙሃንን ነፃነት ማረጋገጧን እና የተዘጉ ድረገፆችን መክፈቷን ለአብነት አንስተዋል።

በተጨማሪም በካቢኔ ደረጃ ሴቶች 50 በ50 በሆነ መንገድ ወደ ስልጣን መቀላቀላቸውንም አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ነጻ  ቪዛ  አገልግሎት በመሥጠት  ከአፍሪካ  የመጀመሪያ  አገር  በመሆኗ  ለሌሎች  አገራትም ተምሳሌት  ለመሆን  መቻሏን  ዶክተር አብይ  በስብሰባው ተናግረዋል ። 

በዛሬው ዕለት በተጀመረው የመሪዎቹ አስቸኳይ ጉባኤ የህብረቱ ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ መሃማት እና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ፖል ካጋሚም በስብሰባው ትኩረት ዙሪያ ንግግራቸውን አድርገዋል፡፡